ባለሃብቶችና ላኪ ድርጅቶች የኢኮኖሚ አሻጥርን እንዲከላከሉ ተጠየቀ

57

አዲስ አበባ ጳጉሜን 3/2013 (ኢዜአ) ባለሃብቶችና ላኪ ድርጅቶች ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ኢኮኖሚያዊ አሻጥርን እንዲከላከሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ የምታገኘው የምንዛሬ መጠን ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች ዋጋ 15 በመቶ እንኳን ባለመሸፈኑ ዘርፉ ትልቅ ስራን የሚጠይቅ ነው ተብሏል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በወጪ ንግድ የላቀ አፈፃፀም ላሳዩ 41 ከፍተኛ ላኪ ኩባንያዎች ትናንት ማምሻውን የሽልማትና ዕውቅና ማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷቸዋል።

ኩባንያዎቹ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት፣ የጥራጥሬ እህሎች፣ ስጋ፣ የቁም እንስሳት፣ ጨርቃጨርቅ፣ ማዕድን፣ ምግብና መድሀኒት፣ ኮንስትራክሽንና ኬሚካል ምርቶችን ጨምሮ በ18 ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበጀት ዓመቱ የአገር ውስጥ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ 3 ነጥብ 64 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱንና በዘርፉ የተያዘውን ዕቅድ 88 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ አገሪቷ የገጠሟትን የውጭና የውስጥ ጫና ጨምሮ በኮሮና ወረርሽኝ ተፅእኖም ዘርፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ በተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ ውጤታማ የሚባል አፈፃፀም ተገኝቷል ብለዋል።

ለአብነትም በጥቂት ምርቶች ብቻ ተወስኖ በገበያ መዋዥቅ ሲጎዳ የቆየውን የወጪ ንግድ በመጠን፣ በአይነትና በመዳረሻ በማስፋት በታሪክ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘት መቻሉን አንስተዋል።

በቀጣይም የአፍሪካን የገበያ መዳረሻ በማስፋት፣ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ ዘመናዊ ግብይት በመተግበርና ኮንትሮባንድን በመከላከል ዘርፉን ዘላቂና ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚያሳድጉ ስራዎች ላይ እናተኩራለን ብለዋል። 

በሚኒስቴሩ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድም ከዘርፉ 18 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት መታቀዱን አመልክተዋል።

በቀጣዩ የ2014 በጀት ዓመት አዳዲስ ምርቶችና መዳረሻዎችን የማስፋት፣ የአሰራር ማነቆዎችን የመፍታትና የማዘመን ስራ ላይም ትኩረት ይደረጋል ብለዋል ሚኒስትሩ። 

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምርት ብክነትን መቀነስ፣ የምርት ጥራትን ማሳደግ፣ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ወደ ገበያ ማስገባት እንደሚገባም አንስተዋል።

ለአገሪቷ ጤናማ ዕድገት የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙና የሚያሳድጉ መስኮችን ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ወጪ ምርቶችን ተቋማዊ በሆነ አግባብ በማሳደግ በተለይ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛኑን እንዲጠብቅ በማድረግ ዘርፉን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።

አሁን ያለው የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ሰፊ ክፍተት እንዳለበት ጠቁመው፤ በወጪ ንግድ የሚገኘው ምንዛሬ ኢትዮጵያ ከምታስገባቸው ምርቶች ዋጋን 15 በመቶ እንኳን አይሸፍንም ብለዋል።

ይህ እንደ አገር ትልቅ የኢኮኖሚ ጦር ግንባር ተደርጎ ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት።

የዕውቅና መርሐ ግብሩ ዓላማም ተወዳዳሪ የሆኑ ላኪዎችን ለመፍጠርና ለማበረታታት መሆኑን ተናግረዋል። 

ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማሻሻልም ወደ ምርት ያልገቡ ባለሀብቶች ወደ ማምረት በመሸጋገር በወጪ ምርቶች መጠንና ጥራት በዓለም ገበያ እንዲወዳደሩ፣ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩና አገራዊ ምርት እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል።

ባለሃብቶችና ላኪ ድርጅቶችም አገሪቷ ውስጣዊና ውጫዊ ጦርነት በተቃጣባት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ኢኮኖሚያዊ አሻጥርን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል።

እናቶች ልጆቻቸውን ለአገር ህልውና በሚልኩበት ወቅት በየቦታው በኢኮኖሚ አሻጥር ሕዝብን የሚጎዱ አካላትን በጋራ ልንታገል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም