ቀጥታ፡

የአብሮነት እሴቶቻችንን በማጠናከር የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል.. ዶክተር አህመዲን መሐመድ

ደብረ ብርሃን፤ ጷጉሜን 3/2013 (ኢዜአ) አብሮ የመኖር፣ የመደጋገፍ እና የአንድነት እሴቶቻችንን በማጠናከር የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ተናገሩ።

በአጣዬ ከተማ ተከስቶ በነበረ የጸጥታ ችግር ቤት ንብረታቸው ለተቃጠለባቸው ግለሰቦች ከ3 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ መጠለያዎች ተሰጥቷል።

በመጠለያዎቹ ርክክብ ወቅት የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ቀጣናውን በማተራመስ የቆየውን የህዝቦች አንድነት ለመሸርሸር እየሰሩ ነው።

በአጣዬና አካባቢው የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአርጎባና የአፋር ህዝቦች በአንድነት ተዋደውና ተደጋግፈው ለዘመናት የኖሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

"የህዝብ አንድነትና ሰላም የማይዋጥላቸው የጥፋት ሀይሎች በአካባቢው በፈጠሩት ግጭት በርካታ ዜጎች ህይወታቸው አልፏል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግርም እየተዳረጉ ነው" ብለዋል።

አብሮ የመኖር፣ የመደጋገፍና የአንድነት እሴቶቻችንን በማጠናከርም ሀገራችን አሁን ከገጠማት የህልውና ችግር ፈጥና እንድትወጣ  ልንረባረብ ይገባል ነው ያሉት ዶክተር አህመዲን።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ በበኩላቸው፤ከአጣየና አካባቢው ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለተፈናቃዮቹ የእለት ደራሽ ምግብና አልባሳት ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ሲደረጉ መቆየቱን ጠቁመው፣ ቀሪ ስራዎች ስላሉ የወገን ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በአጣዬና አካባቢው ህብረተሰቡ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በአካባቢው ጽንፈኛ ሃይሎችን አጋልጦ ለህግ እንዲቀርቡ በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀስ ይኖርበታል" ብለዋል። 

የአጣዬና አካባቢው ኮማንድ ፖስት ሃላፊ ሌተናል ጄነራል ደስታ አቢቼ፤ ሀገርን ለማፍረስ  የተሰማራውን የህወሓት የሽብር ቡድንና ተላላኪዎቹን ለመደምሰስ በተደረገው ጥረት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

"ህዝቡ በግንባር ላለው ሠራዊትም ይሁን በአጣዬና አካባቢ ያለውን ሰላም እንዲረጋገጥ እያደረገ ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ሰላም ፈላጊነቱን ያሳያል" ብለዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ ሸኔ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎችን በማሰስ ለማጥፋት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ህዝቡ ጸረ ሰላሞችን በማጋለጥ የጀመረው እገዛ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። 

በከተማዋ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው 64 የድሃ ድሃ አባውራዎች የመኖሪያ መጠለያዎች መገንባታቸውን የአጣየ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አገኘሁ መክቴ ገልጸዋል። 

መጠለያዎቹ የተገነቡት ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከህብረተሰቡ በተዋጣ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከህዝቡ በተሰበሰበ ገንዘብ የመኝታ ፣ የምግብ ማብሰያ እቃዎች፣ የሌሊት አልባሳትና ሌሎች ቁሶች ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

እንዲሁም መኖሪያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው ሌሎች 45 ግለሰቦችም መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ነው አቶ አገኘሁ ያመለከተቱት።

እንደእሳቸው ገለጻ፤ የቤቶቹ ግንባታ በቀጣይ ሁለት ወራት ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ።

መጠለያ ቤት ካገኙት መካከል ወይዘሮ አልማዝ መታፈሪያ በሰጡት አስተያየት ''በኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን እየተደረገልን ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ትናንት የነበረውን ችግር ረስተን በአዲስ መንፈስ ለሥራ እንድንነሳሳ አግዞናል'' ብለዋል። 

በመጠለያዎቹ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራል፣ ዞንና ከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ተጠቃሚ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም