በአርባ ምንጭ ከተማ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 162 የንግድ ድርጅቶች ታሸጉ - ኢዜአ አማርኛ
በአርባ ምንጭ ከተማ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 162 የንግድ ድርጅቶች ታሸጉ

አርባ ምንጭ ፤ ጷጉሜን 03/2013(ኢዜአ) በአርባ ምንጭ ከተማ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 162 የንግድ ድርጅቶች እንዲታሸጉ መደረጉን የከተማዋ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የንግድ ድርጅቶቹ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉት ጤፍና ጥራጥሬን ጨምሮ በተለያየ የምግብ እህል እንዲሁም በፋብሪካ ውጤቶች እንደ ማካሮኒ፣ ፓስታ፣ ሩዝ፣ ዘይት፣ ዱቄትና የህንፃ መሣሪያዎች ላይ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወይዘሮ ዮርዳኖስ ወንድይፍራው ለኢዜአ ተናግረዋል።
ጽህፈት ቤቱ ከጸጥታ አካላት ጋር ለሁለት ሳምንት ባደረገው ጥናት ከ20 ብር እስከ 200 ብር በኪሎ ግራምና በዓይነት ጭማሪ መደረጉን እንደተረጋገጠ ገልጸዋል።
በዚህም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ 162 የንግድ ድርጅቶች እንዲታሸጉ መደረጉን አሰታወቀዋል።
እንዲሁም በአንድ ግሮሰሪ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ለጊዜው መጠኑ ያልታወቀ ቅቤ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጠቁመዋል።
ይህን ጊዜ ተደጋግፈን ማለፍ ሲገባ ህዝብን ያለአግባብ መበዝበዝ ከአሸባሪው ህወሃት የጥፋት ተግባር ለይተን የማናየው ጉዳይ ነው ያሉት ሃላፊዋ፤ የታሸጉት የንግድ ተቋማት ጉዳይ ተጣርቶ በህግ እንደሚጠየቁ ነው የገለጹት።
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አረጋሽ ክብሩ በሰጡት አስተያየት፤ በበዓሉ የሚፈለጉ ምርቶችን እየደበቁ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር የተጋነነ ዋጋ የሚጨምሩ የንግዱ አካላት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በተለይ እየጎዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማዋ በቆሎ አንድ ኪሎ ከ13 ብር ወደ 30፣ ዱቄትና ማካሮኒ ከ30 ብር ወደ 60፣ ዘይት ከ500 ወደ 700 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል።
ሁሉም ነጋዴዎች በሃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አመልክተው፤ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ጠጁ አስፋው በበኩላቸው፤ ባያዋጣም የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤቱ ባወጣው ተመን እየሸጥኩ ነው ብለዋል።
ከምንም በላይ የገበያ ስርዓት የሚያመሰቃቅሉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በመሆናቸው የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
ለእያንዳንዱ ዕቃ ዋጋ ዝርዝር አውጥተን እንድንሸጥ እየተደረገ ያለው አሠራር ተገቢ ነው ያሉት ደግሞ በከተማዋ የህንፃ መሣሪያ ነጋዴ የሆኑት አቶ ሽኩር ጀሚል ናቸው።