በህገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ ከ80 ሺ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ ከ80 ሺ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ
ጳጉሜን 3/2013 (ኢዜአ) ያልተገባ የዋጋ ጪማሪ ያደረጉና በህገወጥ ተግባር የተሳተፉ ከ80ሺ በላይ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በኢፌዲሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ አቶ ወንድአጥር መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ በህግ ማስከበር ዘመቻው እየተገኘ ያለውን ድል ለመቀልበስ በህገወጥ ተግባራት የተሳተፉ የንግድ ተቋማትን እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ወንድአጥር ገለጻ ፤ ዶላርና ምርት የደበቁ፣ ያልተገባና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሬ በማድረግ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈትሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡
እርምጃ ከተወሰደባቸው 80ሺ641 የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ፣ 5 መቶ 20 የንግድ ድርጅቶች የንግድ ፈቃድ ስረዛ፣ 2 መቶ 57 የንግድ ድርጅቶች ላይ የእገዳ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን አቶ ወንዳጥር ጠቁመው በ2ሺህ 230 የንግድ ተቋማት ላይ ክስ መመስረቱን ተናግረዋል፡፡
አቶ ወንዳጥር እንደገለጹትም፣ ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያትና የአቅርቦት ችግር ያልተገባ ዋጋ በመጨመር ህገ ወጥ የሆነ ገንዘብ ለማጋበስ የሚሰሩ መኖራቸውንና በተለይም የህግ ማስከበር ዘመቻ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት በዚህ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ አካላትን መንግሥት አይታገስም፡፡
ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከመረጃና ደህንነት፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ በሚኒስትሩ የሚመራ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ እየተሰራ ነው ያሉት የኮሙኒኬሽን አማካሪው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ምንጭ-(ኢ ፕ ድ)