ዳያስፖራው የሚያደርገውን ጉብኝት የሚያስተባብር የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው የሚያደርገውን ጉብኝት የሚያስተባብር የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ
ጳጉሜ 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የሚያካሂዱት ጉብኝት የሚያስተባብር የልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ገባ።የልዑካን ቡድኑ ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የቱሪዝም ኢትዮጵያ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት ባዘጋጀው "እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ መርሃ ግብር ከጳጉሜን ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚካሄድ ነው።
ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት መርሃ ግብሩን የሚያስተባብሩት ስድስት የምክር ቤቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ናቸው።በመርሃ ግብሩ ከሰሜን አሜሪካ፣ እስያ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ የሚመጡ 500 ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ነው።
በመርሃ ግብሩ ዳያስፖራው "አባይን እንጎብኘው" በሚል መሪ ሀሳብ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ እንደሚጎበኝና የግድቡን ሰራተኞች እንደሚያበረታቱም ይጠበቃል።የሸገር ማስዋብና በገበታ ለአገር ፕሮጀክት የተካተተው ጎርጎራ የጉብኝቱ አካል እንደሚሆንም ተነግሯል።