መልካምነት ለማንኛውም ህይወት እና ስነ-ምግባር መሰረት ከመሆን ባለፈ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መልካምነት ለማንኛውም ህይወት እና ስነ-ምግባር መሰረት ከመሆን ባለፈ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው

ጳጉሜን 3/2013(ኢዜአ) “መልካምነት ለማንኛውም ህይወት እና ስነ-ምግባር መሰረት ከመሆን ባለፈ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው” ሲሉ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ዛሬ ጳጉሜን ሶስተኛ የመልካምነት ቀንን አስመልክተው ምክትል ከንቲባ አዳነች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የመልካምነት መገለጫ ለእያንዳንዳችን ስኬት፣ እድገት እና ድል ወሳኝ ግብዓት ነው ብለዋል።
የመልዕክቱ ሙሉ ሀሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
-----------------------------------------------------------------------
ክቡር/ክቡራን
ውድ የከተማችን ነዋሪዎች
ክቡራትና ክቡራን
ከዋሻው ጫፍ ላለው ብርሃን ስክነት እንዲሆን መልካም ምግባረኞች ያስፈልጋሉ፡፡ ዛሬ በጳጉሜን ሶስተኛ ቀን ላይ ሆነን የመጪው ዘመን ተምሳሌትነትን የምንሰጠው ለመልካምነት ነው፡፡
መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይልቃል፡፡ መልካም ስምን የሚወልደው መልካም ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም መልካም ተግባር በርካቶችን ማሰባሰብ የሚችል ግሩም የተግባር መዓዛ ነው፡፡ መልካም ለመሆን የግድ ሃብት አያስፈልግም፤ እውቀትም የግድ አይደለም፤ ቅን መሆን መልካምነትን ያጸናዋል፡፡ መልካምነት የዘለቀ ብርሃን ሆኖ እንዲወጣ ሰው የተፈጠረበትን ዓላማ ማወቅ ከቻለ ለመልካምነት የበለጠ ይሽቀዳደማል፡፡
መልካምነት አዝመራ ነው፡፡ የህይወት ጎተራን የሚሞላ ለአገር የሚተርፍ ተግባር ነው፡፡ አንድ ገበሬ ዘሩን ከመሬት ስላገኘ ብቻ ፍሬ አያገኝም፤ ብርቱ ክትትልና ትጋትን ይጠይቀዋል፡፡ መልካምነትም ማሰብ ብቻውን አይበቃውም፤ አብዝቶ ከመልካም ስራዎች ጎን መሰልፍን፣ ሌሎችን ማገዝ ላይ ማትኮርን፣ ከራስ በላይ ለሌሎች ማድረግን፤ ይፈልጋል፡፡
መልካምነት ለማንኛውም ህይወት እና ስነ-ምግባር መሰረት ከመሆን ባለፈ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው፡፡ ይህ መገለጫ ለእያንዳንዳችን ስኬት፣ እድገት እና ድል ወሳኝ ግብዓት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደተቋም መልካምነትን በማወጅ ብቻም ሳይሆን በማድረግም ተሳትፎ አድርገቷል፡፡ ከነዚህም ተግባራቱ መካከል ማዕድ ማጋራት፣ ደም መለገስ፣ የምገባ ማዕከል ማቋቋም፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ማደስና መደገፍ እና የመሳሰሉ በርካታ መልካምነት ላይ ያተኮሩ ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ይህን ሲሰራ ብቻውን ያከናወነው አይደለም፡፡ ከነዋሪው እና በጎፈቃደኞች ጋር በመተባበር የሰራቸው የምልካምነት መታያ የሆኑ ስራዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በቂ አይደሉም፡፡ መልካምነታችን የሚያስፈልጋቸው በርካታ ወገኖቻችን አሉ፡፡ ቤታቸውን ልንሰራ፣ ማእዳቸውን ልንሞላ፣ ጤናቸውን ልንጠብ፣ እውቀት ብርሃንን ልናሳያቸው፤ የሚገቡን ወገኖቻችን ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ከተባበርን በመልካም ተግባራት ላይ ከተረባረብን ለበርካቶች መድረስ እንችላለን፡፡
የድላችን ሚስጥር መልካምነታችን መሆኑን እናስታውስ፡፡ መጪውን 2014 ዓመት ስንቀበል ኢትዮጵያዊ መልካምነታችንን በተግባር እያከበርን በማጠናከር እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ የመልካም ሰዎች ቁጥራቸው ይብዛልን፡፡ መልካምነት ለራስ ነው፡፡
መልካም በዓል፡፡
አመሰግናለሁ፡፡