ቀጥታ፡

አካል ጉዳተኞች በፍድ ቤቶች የተሻለና ተገቢ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ አሰራሮች ተዘርግቷል

አካል ጉዳተኞች በፍድ ቤቶች የተሻለና ተገቢ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ማዓዛ አሸናፊ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር 20ኛ ዓመቱን ዛሬ አክብሯል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መዓዛ አሸናፊ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አካል ጉዳተኞች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበር በፈርድ ቤቶች በኩል እየተሰራ ነው።  

በፍርድ ቤቶች በሚካሄዱት የአሰራር ማሻሻያ ሥራዎች አካል ጉዳተኞች ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ አገልግሎቶችን ያለምንም ችግር እንዲያገኙ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቶ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

አካል ጉዳተኞች ሚዛናዊና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲየገኙ መመሪዎችም መሻሻላቸውን ጠቁመዋል።

በቅርቡ በጸደቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶችን አዋጅ ቁጥር 1234 ውስጥ አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ  አንቀጾች መካተታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ፍርድ ቤቶች ፍትሃዊነትና ገለልተኛነታቸውን ወደ ጎን ሳይሉ ለአካል ጉዳተኞች አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋየ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በተለይም የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለመፍታት የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ጭምር የማጠናከር ሥራ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ድባቤ ባጫ አካል ጉዳተኞች መብታቸው ለማስከበር ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለዚህም ማኅበሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል በአካል ጉዳተኛ ሴቶች ላይ የሚደረሰውን አድሎና መገለል ለመቀነስ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ማኅበሩ የመሥሪያ ቦታ አለመኖሩን ጠቁመው የሚመለከተው አካል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ለማኅበሩ የመስሪያ ቦታ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ማኅበሩ ድጋፍ ላድረጉለት ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና ሰጥቷል፤ ሽልማትም አበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም