የአፋር ክልልን እንደመሸጋገሪያ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢሞክርም አልተሳካለትም - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልልን እንደመሸጋገሪያ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢሞክርም አልተሳካለትም
ዻጉሜን 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት የአፋር ክልልን እንደመሸጋገሪያ በማድረግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢሞክርም የአፋር መሬት መቀበሪያው እየሆነ መምጣቱን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ገለጹ፡፡
የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፣ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ይታያል ገላው በተገኙበት ከአማራ ክልል የተወጣጡ ባለሃብቶች ለአፋር ክልል የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ዛሬ ባለሃብቶቹ ድጋፉን ሲያስረክቡ፤ በኢትዮጵያ አንድነትና ክብር ዙሪያ "ከማይደራደረው የአፋር ህዝብ ጎን በመቆማችን ኩራት ይሰማናል" ብለዋል፡፡
በርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ አበባው ደስታ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ከመከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን "ሌተ-ቀን እየተዋጋ ከሚገኘው የአፋር ህዝብ ጎን በመቆም አሸባሪውን ቡድን ድል እናደርገዋለን" ብለዋል፡፡
የአፋር ክልል ህዝብ ኢትዮጵያን ለማዳን እያደረገ የሚገኘውን ተጋድሎ ለማገዝና የተፈናቀሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማቋቋም የሚውል የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የአማራ ባለሃብቶች አድርገዋል።
አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያዊያን ለነጻነታቸው የማይተኙ ህዝቦች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያን "ከአሸባሪው ትንኮሳ ነጻ በማድረግም ወደ እድገት ጎዳና እንጓዛለን" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አንድነት እስከሚጸና እና ዘላቂ ሰላም እስከሚመጣ ድረስም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳዳር አቶ አወል አርባ ባለሃብቶቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አሸባሪው ሕወሃት ኢትዮጵያን በመራበት ወቅትም "በሽፍትነት ተግባር ላይ የተሰማራ ነበር" ያሉት ርዕሰ መስተዳዳሩ፤ ይህን ሃይል ለማጥፋት መተባበር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
አሸባሪው በድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የአፋር ክልልን እንደመሸጋገሪያ ለመጠቀም ቢሞክርም "የአፋር መሬት መቀበሪያው ሆኗል" በማለት ያሰበው እንዳልተሳካለት ገልጸዋል።
ባለሃብቶቹ ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪም አቶ ወርቁ አይተነው በግላቸው 50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
በተጨማሪም ባለሃብቶቹ 400 ሰንጋ በሬዎችን በመግዛት በአፋር ግንባር ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት የበዓል መዋያ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
የአፋር ክልል መንግስትም ለባለሃብቶቹ የክልሉን ባህላዊ ልብስ አበርክቷል።