"ከሃዲና ባንዳዎች በኢትዮጵያ ምድር ተመቻችተውና ተደላድለው ኖረው አያውቁም" - ኢዜአ አማርኛ
"ከሃዲና ባንዳዎች በኢትዮጵያ ምድር ተመቻችተውና ተደላድለው ኖረው አያውቁም"
አዲስ አበባ፣ ጷጉሜ 2/ 2013 (ኢዜአ) ከሃዲና ባንዳዎች በኢትዮጵያ ምድር ተመቻችተውና ተደላድለው ኖረው አያውቁም፤ ወደ ፊትም አይኖሩም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
የብርሸለቆ መሰረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ34 ጊዜ ያሰለጠናቸው መሰረታዊ ወታደሮች አስመርቋል።
በመርሃ ገበሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ከተዘጋጁ የቁርጥ ቀን ልጆች ጋር መገኘት ትልቅ ክብር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለክብር የሚሞቱ የቁርጥ ቀን ልጆች እያፈራች የኖረች ስትሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሃዲና አሸባሪዎችም የዚሁ ታሪክ አካል ሆነው ቆይተዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ሆኖም ከሃዲና ባንዳዎች በኢትዮጵያ ምድር ብቅ ብለው ይጠፋሉ እንጂ ተመቻችተውና ተደላድለው ኖረው አያውቁም ወደ ፊትም አይኖሩም ነው ያሉት።
የዛሬ ተመራቂዎችም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የገጠማትን ጠላት ለመመከት አገራዊ ስምሪት ለመቀበል መዘጋጀታቸው ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የምትቀጥል አገር መሆኗን ለጠላትም ለወዳጅም ያሳየ ነው ብለዋል።
''እነዚህን የታሪክ እፉኝቶች ከአገር ጫንቃ ላይ ለቅሞ ለማውረድ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር ተንቀሳቅሷል፤ ታሪካዊ ደጀንነቱንም እያሳየ ነው'' በማለት ገልጸዋል።
ህይወታቸውን ሰጥተው አገር ለማዳን የተሰለፉ የኢትዮጵያ ልጆች ዝግጅት ጠላትን ከወዲሁ እያራደ ይግኛል ያሉት አቶ ደመቀ ''ኮርተንባችኋል፣ እጅግ አናከብራችኋለን'' ብለዋል።
የምድር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ብቃት ጠላቶችም ወዳጆችም የመሰከሩለት መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬም ቢሆን የእናት ጡት ነካሽ የሆነውን የህወሓት አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት ሰራዊቱ ውጤታማ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን ገልፀዋል።
አሸባሪው ህወሃት በሰሜንና በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም በአፋር ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አሰቃቂ ተግባር መፈፀሙን አንስተዋል።
በመሆኑም ይህን አገር አፍራሽና ከሃዲ ቡድን የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት ለማጥፋት ቁርጠኛ ሆና እየተገለ መሆኑን ገልጸዋል።