ቀጥታ፡

ኢቢሲ ለተፈናቃዮች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ደሴ፣ ጷጉሜን 2/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህልና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ኮርፖሬሽኑን በመወከል ዛሬ ደሴ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት አቶ አቤል አዳሙ እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ከጎናቸው ሆኖ ማገዝ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

ኮርፖሬሽኑ 350 ኩንታል በቆሎ፣ 100 ኩንታል ስንዴ፣ 800 ብርድ ልብስና 20 ቦንዳ የተለያዩ አልባሳትን በድጋፍ ማስረከቡን ተናግረዋል ።

ድጋፉ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው መሆኑን አመልክተዋል።

በአፋርና በጎንደር ለተጠለሉ ተፈናቃዮችም ድጋፍ ማድረጋቸውን  ጠቅሰዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ህብረተሰቡን በማንቃትና ወቅታዊ መረጃ ለማድረስ ከሚሰራቸው ዘገባዎች ባለፈ የጀመረውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው ህብረተሰቡንና የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር በአሸባሪው ቡድን ተፈናቅለው ደሴ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ከመንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከህብረተሰቡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።

ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ድጋፍ ለወገን ያለውን አጋርነት ያረጋገጠበት መሆኑን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል ።

ኮርፖሬሽኑ በአሸባሪው ህወሀት ወረራ ከአማራና ከአፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች አጠቃላይ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ በወቅቱ ተገልጻል ።

በአሸባሪው ህወሓት ተፈናቅለው በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የተጠለሉ ወገኖች ቁጥር ከ223 ሺህ በላይ ስለመድረሱ መመላከቱን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም