ቀጥታ፡

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት" በሚል መሪ ሐሳብ የወጣቶች ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

ጳጉሜን 2/2013 (ኢዜአ) "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት" በሚል መሪ ሐሳብ የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፈራረስ እቅድ ለማጋለጥ ከመስከረም 3 እስከ 15 ቀን 2014 ዓ.ም የወጣቶች ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።

የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አትሌቶች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የኃይማኖት  መሪዎች፣ ምሑራን  እና  ሌሎች  ታዋቂ ግለሰቦች በንቅናቄው እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የአሸባሪውን ህወሓት አገር የማፍረስ ወረራን ማጋለጥ፣ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ግፍ ማሳየት፣ የሽብር ቡድኑ በኢትዮጵያዊያን የተጠላ መሆኑን ማሳወቅ የንቅናቄው ዋና አላማ ይሆናል።

የመንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔና የአሸባሪው ቡድን ምላሽ፤ ቤተ-እምነቶችን ጨምሮ በጤና እና ሌሎች ማህበራዊ ግልጋሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያደረሰውን ውድመትና ዘረፋም እንዲሁ ማሳየት።

የኢትዮጵያ ዩዝ ኢንፓወርመንት ማኅበር እና አገር አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄ አስተባባሪ ወጣት ዓለማየሁ ሰይፉ፤ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ጫና መቃወም የንቅናቄው ሌላኛው ዓላማ መሆኑን አስረድቷል።

የንቅናቄው ምክትል አስተባባሪ ወጣት አክሊሉ ታደሰ፤ አሸባሪው ህወሃት በታቀደ መንገድ ኢትዮጵያን መበተን ዓላማ አድርጎ ባለፉት 30 ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሷል።

በመሆኑም አሸባሪው ሃይል በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን የረጅም ጊዜ የጥፋት እቅድ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግልጽ ሊረዳው ይገባል ብሏል።

አሸባሪው ህወሃት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጦርነት ሲከፍት መቆየቱንና በሰሜን ዕዝ የፈጸመውን ዘግናኝ እልቂት ለአሜሪካና ቀሪው ዓለም በአግባቡ ማሳወቅም ሌላኛው ግብ መሆኑን ተናግሯል።

 "የነጩ ጎርፍ ፖስታ ለነጩ ቤተ-መንግሥት" የፖስታ መልዕክት  ለአሜሪካው  ፕሬዚዳንት  ጆ ባይደን እንዲደርስ ይደረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም