ቀጥታ፡

አሸባሪውን ዋሻ ማስገባት ሳይሆን እስከ መጨረሻው ደምስሶ ለመቅበር በቅንጅት እየተሰራ ነው

ደሴ፤ ጷጉሜን 2/2013(ኢዜአ) አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ቦታ አስለቅቆ ዋሻ ውስጥ ማስገባት ሳይሆን ዳግም አንገቱን ቀና አድርጎ እንዳይነሳ ደምስሶ ለመቅበር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ተናገሩ።

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በደሴ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት ዶክተር አለሙ ስሜ እንደገለጹት፤  አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሃይማኖትንና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ በመከፋፈል እርስ በእርስ እንዲጠራጠር አድርጎታል፡፡

በሁሉም ክልሎች እንደ ሸኔ ያሉ  የህዝብ ጠላት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ በስውርና በግልጽ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ይባስ ብሎ አሁን ላይ በይፋ ከጠላቶቻችን ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለማዋረድ እየሰራ ነው፡፡

ቡድኑ እድሜ ልኩን የሰራው ግፍ፣ በደል፣ ሰቆቃ፣ ዝርፊያና ውንብድና  አልበቃው ብሎ መከላከያ ስራዊቱን ከጀርባው መውጋቱን ያወሱት ዶክተር አለሙ፤ በዚህም የተቆጣው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ ዋሻና ጉሬ ውስጥ እንዳስገባው ጠቅሰዋል፡፡

የቡድኑ ርዝራዥ በመንግስት የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በህዝብ ላይ  ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ህብረተሰቡን አሳትፎ ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ ፈፅሞ ስጋት በማይሆንበት መልኩ  በቆፈረው ጉድጓድ ለመቅበር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንን ተናግረዋል።

ይህን የሽብር ቡድን ዋሻ ውስጥ አስገብቶ መመለስ ሳይሆን ዳግም አንገቱን ቀና አድርጎ እንዳይነሳ ከነተላላኪዎቹ ጋር መቅበር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ከኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ ጠላት ከሸኔ ጋር ወግኖ ሀገር ለማጥፋት የጀመረው ሴራም በየትኛውም መንገድና መለኪያ አይሳካለትም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ  ክንዱን ሲያሳርፍበት የወረራቸውን ቦታዎች ለቆ እየፈረጠጠ ነው ብለዋል ዶክተር አለሙ ፡፡

በተለያዩ አካባቢያዎች ጠፍጥፎ በሰራቸው የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች በወሎ በኩል አራት ኪሎ ለመግባት ያደረገው መፍጨርጨር በጀግኖች የኢትዮጰያ ቆራጥ ልጆች  አይቀጡ ቅጣት ተከናንቦ ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።

የወሎ አርሶ አደርና ወጣት ለሰራው አኩሪ ገድል መንግስት እጅጉን ያመሰግናል ያሉት ዶክተር አለሙ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በወኔ በመትመም የአደዋን ታሪክ እየደገመ  ሀገርን ለማስቀጠል ያሳየው አንድነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

ወያኔን   በአካል መቅበር ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡንም ከምድረ -ገፅ ማጥፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት በሪሁን ፀጋየ ፤ የመንግስትን አቅጣጫ ተቀብሎ ቡድኑን ዋሻ ለማስገባት ሳይሆን ለመቅበር እየተካሄደ ባለው ትግል ለመሳተፍ ቆርጦ መነሳቱን ተናግሯል።

አሸባሪው ህወሃት ከውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች ጋር ሀገር ለማፍረስ ያለ የለለ አቅሙን አሟጦ ቢጠቀምም ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፎ  መውጫ ቀዳዳ በማሳጣት ለመደምሰስ የድርሻውን እንደሚወጣ ነው ወጣት በሪሁን የገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም