የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ለአገር መከላከያ ሠራዊት 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ለአገር መከላከያ ሠራዊት 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ለአገር መከላከያ ሠራዊት 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራአስፈጻሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው ሠራዊት 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
በቀጣይም ድጋፍና እገዛው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ተቋሙ ቀደም ሲል የነበረውን የአሰራር እና የአደረጃጀት ክፍተቶች ለይቶ በማስተካከል የተለያዩ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 96 ነጥብ 7 በመቶ የእቅድ አፈጻጸም ክንውን በማድረግ ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።
በድርጅቱ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሠራተኞች የእውቅና ሽልማት የተሰጠ ሲሆን በቀጣይም ለላቀ ስኬት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በመከላከያ ሚኒስቴር የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብራጋዴል ጄነራል አስረስ አያሌው፤ አሸባሪው ህወሓት ከውጭ እና ከውስጥ ጠላቶች ጋር በመሆን አገር ለማፈራረስ የሚያካሂደውን እኩይ ተግባር ሠራዊቱ በመመከት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ህዝቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የላቀ መሆኑን ጠቅሰው ሰራዊቱ እያስመዘገበ ላለው ድል ትልቅ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ከዚህ በፊት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በሀገሪቱ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያለባቸውን የግብአት አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየሠራ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
በድጋፍ እና የእውቅና መርሃ-ግብሩ ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እና ሚኒስትር ዴኤታው ተካ ገብረየሱስ ተገኝተዋል።