እየተደረገልን ያለው ድጋፍ በጀግንነት እንድንዋደቅ አቅም ሆኖናል - ኢዜአ አማርኛ
እየተደረገልን ያለው ድጋፍ በጀግንነት እንድንዋደቅ አቅም ሆኖናል
ሀዋሳ ፤ ጷጉሜን 2/2013(ኢዜአ) ከጫፍ እስከጫፍ በኢትዮጵያዊያን እየተደረገልን ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ በጀግንነት እንድንዋደቅ አቅም ሆኖናል ሲሉ የደቡብ ዕዝ መከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ ፡፡
ከአባላቱ መካከል የዕዙ የሴቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ኮሎኔል ፋንታነሽ ሞላ ፤ መከላከያ ሰራዊቱ ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማዳን እየተዋደቀ ይገኛል፡፡
በተለይም አገር ለማፍረስ የሚሰራውን የህወሓት ቡድንና ተላላኪዎቹን ለመደምሰስ በአውደ ውጊያ መስዋዕት በመሆን ላይ ይገኛል፡፡
ኮሎኔል ፋንታነሽ እንዳሉት፤ መላው ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም አቅጣጫ ለዚህ ሰራዊት የሚሆን የገንዘብ፣ ስንቅ፣ ደም ከመለገስ ባሻገር ግንባር ድረስ በመጓዝ በማበረታታት ድጋፍ እያደረገ ነው።
አሁን ላይ ህዝቡ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ በአውደ ውጊያ በጀግንነት እንድንዋደቅ ትልቅ አቅም ሆኖናል ነው ያሉት።
ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች አሰሳ በማድረግ ቡድኑን የመደምሰስ ሥራ በቁርጠኝነት እየፈፀሙ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ህዝቡ በመተባበርና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለው እገዛ እጅግ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ሻምበል በጊዜው እንደግ በበኩላቸው፤ ህወሓት በሥልጣን በቆየባቸው ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በብሔር፣ ጎሳና ሐይማኖት ለመከፋፈል ሲጥር ቆይቶ አሁን ደግሞ በግልፅ ጦርነት በመክፈት የሀገር ጠላት መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።
ይሁን እንጂ መላው ህዝቡ እንደአባቶቹ በአንድነትና በአርበኝነት በመቆም ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ በተግባር ማረጋገጡን ገልጸዋል።
ሰራዊቱ ላቀረበለት ጥሪ አስፈላጊውን ምላሽ በመስጠት ህዝቡ አለኝታነቱን ማሳየቱንም አመላክተዋል።
ህዝቡ እያሳየ ያለው አጋርነት በግንባር ለሚገኘው ሰራዊት ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው ያሉት ሻምበል በጊዜው፤ አሸባሪው ቡድን ተጠራርጎ እስኪጠፋ ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
እኛ በግንባር መስዋዕትነት የምንከፍለው አንድነቷ የተጠበቀና በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያ እንድትኖር ነው ያሉት ደግሞ ሀምሳ አለቃ ይዲዲያ አክሊሉ ናቸው።
ከጫፍ እስከጫፍ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብም እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የተሞላበት ድጋፍም ለአንድነቱ መቆሙን የሚያሳይ በመሆኑ መቀጠል ያለበት ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል።
በሰራዊቱ ውስጥ ያለን ሴት አባላት ጣይቱን ተምሳሌት በማድረግ ከወንድ ጓዶቻችን እኩል ለሀገራችን እንዋደቃለን ብለዋል ሀምሳ አለቃ ይዲዲያ ።