የሲቪል ማህበረሰብ የልዕቀት ማዕከል ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ የልዕቀት ማዕከል ሊገነባ ነው
ጷጉሜ 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ የሲቪል ማህበረሰብ የልዕቀት ማዕከል ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ የሲቪል መሃንዲሶች ማህበር ናቸው፡፡
ማዕከሉ የአፍሪካ የሲቪል ማህበረሰብ የልዕቀት ማዕከል በሚል ስያሜ እንደሚገነባም ተገልጿል፡፡
ማዕከሉ የሲቪል ማህበረሰብ አመራሮችና ባለሙያዎች አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት፣ ችግር ፈች የሆነ ጥናትና ምርም የሚደረግበትና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጥበት ይሆናል ተብሏል ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅማ ዲልቦ ማዕከሉ ሲገነባ የአገሪቱን የልማት ጉዞ ለማሳካት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ኤጀንሲው እስካሁን 1 ሺህ 600 አዳዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን መመዝገቡንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሸን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ማዕከሉ ደረጃውን ጠብቆ እንዲገነባ ዲዛይን በማውጣትና በምህንድስና ስራዎች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ የልዕቀት ማዕከል በኢትዮጵያ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገሪቱ ዴሞክራሲ ግንባታና የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ በእውቀትና በክህሎት ተመስርተው እንዲሰሩ የልዕቀት ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ የበኩላቸውን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሲቪል መህንዲሶች ማህበር ዳይሬክተር ኢንጂነር አማኑኤል መኮንን በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ጠንካራ ማዕከል ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከውጪና ከውስጥ ተፅእኖ ተላቀው መስራት ከቻሉ ለአገር ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡