ሩስያ መርህ ላይ የተመረኮዘ ድጋፍ በመስጠት ሁሌም የኢትዮጵያ አጋር ናት - ኢዜአ አማርኛ
ሩስያ መርህ ላይ የተመረኮዘ ድጋፍ በመስጠት ሁሌም የኢትዮጵያ አጋር ናት
ጳጉሜ 01/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና ሩስያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ ገለጹ።
አምባሳደር ዓለማየሁ ተገኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያና የሩስያ ግንኙነት ታሪካዊና ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ አጋርነት ነው።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለያዩ መንግሥታት ሥር እያደገ በመምጣት አሁን ላይ ፈረጀ ብዙ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳለው ተናግረዋል።
በተለይም ደግሞ የኢትዮ-ሩስያ የጋራ በይነ - መንግሥታት ኮሚሽን መቋቋም ትብብሩና ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር ማስቻሉን ነው የገለጹት።
በምጣኔ ሃብቱ ዘርፍ በሁለቱ አገራት መካከል ከ20 በላይ የሁለትዮሽ ሥምምነት መፈረማቸውን ጠቁመው፤በተለያዩ የትግበራ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ይህም በቅርቡ ኒዩክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ በተለይም ለሃይል ማመንጫነት ለመጠቀም በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ሥምምነትን እንደሚያካትት አብራርተዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍም በርካታ የሩስያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በንግድ ዘርፍም አጋርነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን በመጠቆም።
በሕዝብ ለሕዝብ በተለይም በባህል ዘርፍ ግንኙነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው፤ "ወደ ሩስያ የሚየቀኑት ኢትዮጵያን ተማሪዎችም በዚህ ረገድ ትልቅ አበርክቶ አላቸው" ብለዋል።
በተለያዩ ዘርፎች ላይም ሩስያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንድትሰጥም በእቅድ መያዙን ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም እየተጠናከረ የመጣው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የሩስያ ኦርቶዶክሰ ቤተክርስቲያን አጋርነት ሌላኛው ማሳየ መሆኑን አንስተዋል።
በተጓዳኝም በርካታ የሩስያ ቱሪስቶችም በኢትዮጵያ ጉብኘት ለማድረግ ፍላጎታቸው መጨመሩንም ጠቁመዋል።
በፖለቲካው ዘርፍ ኢትዮጵያና ሩስያ ያላቸው ግንኙነት በባለብዙ ወገን መድረኮችም ላይ መጠናከሩን ገልጸው፤ "ይህም የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
ሩስያ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የመደገፍ ሥራ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሩስያ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አጋርነቷን መሳየቷን አረጋግጠዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር አጋርነቷን በማሳየት ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ መዋሏን ነው የገለጹት።
"ሩስያ መርህ ላይ የተመረኮዘ ድጋፍ በመስጠት ሁሌም ከእኛ ጋር ናት" ያሉት አምባሳደር ዓለማየሁ፤ ይህም አጋርነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክረን እንሰራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያና የሩስያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከ125 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።