ኢትዮጵያዊያን እየለገሱት ያለው ደም ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ሆኖታል--የመከላከያ ደም ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን እየለገሱት ያለው ደም ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ሆኖታል--የመከላከያ ደም ባንክ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜ 1/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ደም በመለገስ ለመከላከያ ሠራዊት እያሳዩት ያለው አጋርነት ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ እንደሆነው የመከላከያ ደም ባንክ ገለጸ።
የመከላከያ ደም ባንክ ሜዲካል ዳይሬክተር ሻምበል ዶክተር ብርሃኑ ካሳይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር በጦር ሜዳ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያውያን ያሳዩት አጋርነት የሚደነቅ ነው።
ህብረተሰቡ ለአገሩና ለወገኑ ህይወቱን እየሰጠ ላለው መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች በገንዘብ፣ በደም ልገሳ፣ በሙያ፣ ግንባር ድረስ በመሄድና በሌሎች ተግባራት የሚያሳየውን አጋርነት አድንቀዋል።
ሁሉም ህብረተሰብ ግንባር ድረስ መሄድ ባይችል እንኳን ባለበት ቦታ ሠራዊቱ በጦርነት ወቅት ለሚያጋጥመው የደም መፍሰስ መተኪያ እንዲሆን ደሙን እየለገሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ደም ባንክ በአንድ ወር ውስጥ በዘመቻ መልክ ለመሰብሰብ ካቀደው ዩኒት ደም በላይ መሰብሰቡን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ያሳየውን አጋርነት ታላቅነት እንደሚያመለክት ጠቁመዋል።
የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አሸባሪው ህወሓት ከሌሎች አገርን የማፍረስ አጀንዳ ካላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ እየተፋለመ ላለው የጸጥታ ኃይል ታላቅ የሞራል ስንቅ እንደሆነው አትተዋል።
የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተደረገ ያለው የህልውና ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ድረስ ህብረተሰቡ ደም በመለገስና በሌሎች ድጋፎች አጋርነቱን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የመከላከያ ደም ባንክ ሜዲካል ዳይሬክተር ሻምበል ዶክተር ብርሃኑ ካሳይ በተለያዩ አካባቢዎች ደም በመለገስ ለሠራዊቱ አጋርነታቸውን ላሳዩ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።