የአሸባሪውን ህወሓት የጭካኔ ክንድ በመቁረጥ ሌሎች ጠላቶቻችን እንዲማሩ ማድረግ ይገባል - ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪውን ህወሓት የጭካኔ ክንድ በመቁረጥ ሌሎች ጠላቶቻችን እንዲማሩ ማድረግ ይገባል - ዶክተር አለሙ ስሜ
ጳጉሜ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) ''አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ ያነሳውን የጭካኔ ክንድ በመቁረጥ ሌሎች ጠላቶቻችን እንዲማሩ ለማድረግ የሁሉም ተሳትፎና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል'' ሲሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ አስገነዘቡ።
የደሴ ከተማ ወጣቶች አሸባሪው ህወሓትን በገባበት የወሎ ምድር ማስቀረት በሚቻልበት ሁኔታና በህልውና ዘመቻው ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል፡፡በውይይቱ የተሳተፉት ዶክተር አለሙ ስሜ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት አማራና አፋር ክልሎችን በመውረር በህዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ ግፍና በደል እየፈጸመ ነው፡፡
ቡድኑ የሚያደርሰውን መከራ በጋራ ለመመከት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ቡድኑ ከገባባቸው አካባቢዎች መውጣት እንዳይችል ህብረተሰቡ የጀመረውን ሁለንታዊ ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
የጥፋት ቡድኑ በተፈጸመበት ጥቃት ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እየደረሰበት መሆኑን ተናግረው፤ "ለሌሎች የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ቡድኑን በመቀጥቀጥ በወሎ ምድር ለመቅበር ከሁላችንም ተሳትፎ ይጠበቃል" ብለዋል፡፡
የወሎ አርሶ አደር ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፎ ደጀንነቱን በተግባር ከማሳየቱም ባለፈ አሸባሪውን ፊት ለፊት እየተፋለመ ህልውናውን እያስቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።አርሶ አደሩ የአባቶቹን ታሪክ በመድገም እየፈጸመ ያለው ጀግንነት የሚደነቅና መቀጠል ያለበት አኩሪ ገድል መሆኑን ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሞት ሽረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከራቸው ይህ የበርካታ ዓመታት ዓላማው እየከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።
"ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ንጹሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመጨፍጨፉም ባለፈ የኖረበትን ዘረፋና ወራዳ ተግባሩን ቀጥሎበታል" ብለዋል።ቡድኑ ሊጥ ሳይቀር ጭኖ ለመውጣት እየታተረ መሆኑን ጠቁመው፤ የዘረፈውን በማስጣል ቡድኑን መቅበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አቶ ገዱ እንዳሉት፤ በአማራና አፋር ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ ጫፍ ህብረቱን አጠናክሮ ተነስቷል።"የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ወጣቱ ወደ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት ተቀላቅሎ መሰልጠንና ህልውናውን ማስቀጠል ይኖርበታል" ሲሉም አቶ ገዱ አሳስበዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንር ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ ሞላ በበኩላቸው "አሸባሪው ቡድን የሁሉም ጠላት በመሆኑ ያለ ልዩነት ተረባርበን ለመደምሰስ የድርሻችንን እየተወጣን ነው" ብለዋል።
ከፖለቲካ በፊት የአገርና የህዝብ ሉዓላዊነት መቅደም ስላለበት አባላትና ደጋፊዎቻቸውን በማስተባበር የቡድኑን ዕድሜ ለማሳጠር እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።"በአገር ጉዳይ ከመንግስት የተለየ አመለካከት የለንም" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ አሸባሪውን ህወሓት በመቅበር ህዝብን ነጻ ለማውጣት የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል ወጣቱ ሠራዊቱን እንዲደግፍ ከማስተባበር ባለፈ በግንባር በመፋለም የአገር ሉአላዊነትን እያስከበረ መሆኑን ተናግረዋል።ወራሪው ኃይል የዘረፈውን ንብረት ከወሎ መሬት ይዞ እንዳይወጣ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
"ህልውናችንን ለማስቀጠል ለሰራዊቱ፣ ለልዩ ኃይሉና ለፀጥታ አባላት ደጀን እንሆናለን" ያለው ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሚሊዮን ደመቀ ነው።ወጣቶች እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመከፈል ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግሯል።
"አሸባሪውን ቡድን እንደመስሰዋለን እንጂ ዳግም በላያችን ላይ የባርነት ቀንበር እንዲጥልብን እድል አንሰጠውም" ያለው ወጣቱ ወደ ልዩ ኃይል ለመቀላቀል መወሰኑን አስታውቋል።