ለውጡን ማህበረሰቡን በማገልገል ለመደገፍ መሰማራታቸውን የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለውጡን ማህበረሰቡን በማገልገል ለመደገፍ መሰማራታቸውን የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ወጣቶች ገለጹ
ደብረብርሃን ነሀሴ 7/2010 የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ ጉዞ ማህበረሰቡን በማገልገል ለመደገፍ መሰማራታቸውን በደብረብርሃን ከተማ ስራቸውን የጀመሩ የሀገር አቀፉ የበጎ ፈቃድ አገልጋይ ወጣቶች ገለጹ፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጡት እነዚህ ወጣቶች ስራቸወን የጀመሩት ደብረብርሃን ከተማ ሲገቡ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከሐረር የመጣው ወጣት ገምቴሳ አደም ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ መሆኑን ገልፆ በማንኛውም የሥራ መስክ ማህበረሰቡን ለማገልገል በአካባቢው መሰማራቱን ተናግሯል፡፡ በቆይታውም ተፋሰስን መሰረት ባደረገ ልማት፣ በጽዳት፣ አረጋዊያን በመንከባከብና ደም በመለገስ ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በእንዲህ ዓይነት ሀገር አቀፍ ተግባር ተንቀሳቅሶ እንደማያውቅ ጠቁሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ ጉዞ በመደገፍ ኢትዮጵያ ፍቅር፣ አንድነትና መረዳዳትን ለማሳየት በመሰማራቱ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጣችውና በመቀሌ ዩንቨርሲቲ የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ምሩቅ ወጣት ቃል ኪዳን አጠቃ በበኩሏ ክልል ሳይወስናት ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በበጎ ፍቃድ ማገልገሏ የመንፈስ እርካታ እንደሚሰማት ተናግራለች፡፡ በልማትና በሌላም ስራ ማህበረሰቡን ከማገልገል ባለፈ ከተለያዩ የሀገሪቱ ህዝብ ጋር እርስ በርስ በመተዋወቅ የባህልና የቋንቋ እሴቶች ልምድ ለመለዋወጥ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ጠቅሳለች፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ወደፊትም አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎቷ መሆኑን ጠቁማ መንግስትም አሁን የጀመረው የመረዳዳትና የመደመር እንቅስቃሴ እንዲገለብት ወሰን በሌለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን ማመቻቸት እንዳለበትም አመልክታለች፡፡ የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ስራ አስፈጻሚ ወጣት ፍጹም ደጀኔ እንዳለው በሀገር አቀፍ ደረጃ በጎ ፍቃድ ከሚሳታፉት ወጣቶች መካከል 231 በክልሉ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ክልሉ ከተንቀሳቀሱት ውስጥም 111 ወጣቶች ባህርዳር ከተማ ቀሪዎቹ ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተሰማሩ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ወጣቶቹ ለ15 ቀናት በሚያደርጉት ቆይታ በከተማ ገጠር እየተዘዋወሩ በትምህርት ልማት ፣ በጽዳት ፣ በደም ልገሳ፣ የአረጋዊያንን ቤት በመጠገንና አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ ያገለግላሉ፡፡ ለወጣቶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከላል ሳህለማሪያም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ አገልግሎት በሚሰጡበት አካባቢ ያለው ህብረተሰቡ በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነቱ ባህሉን ፣ወጉንና ማንነቱን ማሳየት እንደሚኖርበትም አመልክተዋል፡፡ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃን ታዬ በበኩላቸው መንግስት በአዲስ መንፈስ የኢትዮጵያን ወጣቶት በማጣመር ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመው ወጣቶቹ የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡