ቀጥታ፡

ግምቱ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ካናቢስ ተያዘ

ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 01/2013(ኢዜአ) ግምቱ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ካናቢስ የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ መያዙን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡

በኮሚሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፉ የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዴሳ ለማ ለኢዜአ እንዳስታወቁት አደንዛዥ ዕጹ የተያዘው ትናንት ሌሊት በጪጩ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በተደረገ ፍተሻ ነው።

ዕጹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-A23897 አዲስ አበባ በሆነ ተሽከርካሪ ተጭኖ ከመሃል አገር ወደ ኬንያ ሲጓዝ መያዙን ተናግረዋል።

ክብደቱ 780 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ዕፅ ግምቱ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን  አመልክተዋል።

አደንዛዥ ዕጹ በተሽከርካሪው በተጫነ ብሎኬት ሥር ተደብቆ  ሊያልፍ እንደነበር  ገልጸዋል።

ቅርንጫፉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከ184 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው አደንዛዥ ዕፅ መያዙን   ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም