የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አብዮት ግብርናውን ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር ይችላል - ፕሬዝዳንት ሙላቱ

2
አዲስ አበባ ነሀሴ 7/2010 በኢትዮጵያ አሁን ያለው የኢንዱስትሪ አብዮት በጥቂት ዓመታት ግብርናውን ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር እንደሚችል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ። ፕሬዝዳንቱ በዱከም ከተማ በቻይና ባለሃብቶች የሚተዳደረውና 86 የተለያዩ ፋብሪካዎችን የያዘውን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጎብኝተዋል። በቅርቡ የተመረቀው ኤስ ኤስ ፒ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተባለውን የመድሃኒት ፋብሪካ ጨምሮ፣ የብረታ ብረት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ጫማ፣ አልሙኒዬምና ወረቀት ፋብሪካዎችን ጉብኝተዋል። ፕሬዝዳንቱ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ አገሮችን ልምድ በመውሰድና ኢንዱስትሪ መር የግብርና ፖሊሲ በመተግበር በፈጣን የለውጥ ሂደት ላይ ናት። ኢንዱስትሪዎች በውጭ ባለሃብቶች ብቻ መያዛቸው ቀርቶ የአገር ውስጥ ባለሃብቶች መሳተፋቸው የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግር ያቀላጥፈዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ በዚህ የለውጥ ሂደት ከቀጠለች በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የግብርና ስራ ወደ ኢንዱስትሪ እንደሚቀየር እምነታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያን በራሳቸው ፍላጎት በኢንቨስትመንት መሰማራት የሚፈልጎ ግዙፍ ኩባንያዎችን ማግኘት ጀምረናል ሲሉም ተናግረዋል ፕሬዝዳንቱ። የቻይና ባለሃብቶች ቢሾፍቱና ዱከምን የሚያገናኝ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ከተማ ለመገንባት ለመንግስት ጥያቄ ማቅረባቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን ጠንካራ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን በቻይናና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብት በተለያዩ ዘርፎች በጋራ መስራት እንፈልጋለን ብለዋል። በቻይና አምስት መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምርቶችን በማጓጓዝና ቱሪዝምን በማስፋፋት ይበልጥ ቅርበት ይፈጥራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም