የአሁኑ ትውልድ በነጻነት የተረከባትን ሀገር ህልውናዋን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነት አለበት

61

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 1/2013(ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ በነጻነት የተረከባትን ሀገር ህልውናዋን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ የማሸጋገር ኃላፊነት እንዳለበት የኢትዮጵያ አምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት አመራርና ሠራተኞች ገለጹ።

የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች ለህልውና ዘመቻው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው ሞሲሳ "ወጥቶ መግባትም ሆነ ሰርቶ መበልጸግ የሚቻለው ሀገር ስትኖር በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በሀገር ላይ የተቃጣው የህልውና አደጋ መመከት አለበት" ብለዋል።

ከዚህ አኳያ አራት የተቋሙ ሠራተኞች የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ተመዝግበው ተራቸውን እየጠበቁ መሆኑን አንስተዋል።

ሌሎች ሠራተኞችም ለሠራዊቱ ከሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ ስራ በማከናወን አጋርነታቸውን እያሳዩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተቋሙ ሠራተኞች በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ሃይል ምክንያት በአማራና አፋር ክልል ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ከተመዘገቡት የተቋሙ ሠራተኞች አንዱ የሆኑት የጽህፈት ቤቱ የእቅድ ክፍል ባለሙያ አቶ ተገኔ ነጋሽ አባቶቻችን በነጻነት ያቆዩልንን ሀገር መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።

ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ወታደር መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ወደን ሳይሆን ተገደን የገባንበትን ጦርነት ከመከላከያ ጎን በመሆን ድል ማድረግ ይጠበቅብናል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም