ቀጥታ፡

"ጡረታ ስወጣ ሰንደቅ ዓላማዬን ለልጄ ለማስረከብ ከዩኒቨርሲቲ አስወጥቼ ወደ ውትድርና አስገብቸዋለሁ"- ኮሎኔል ደጀኔ ጸጋዬ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1/2013(ኢዜአ) "ጡረታ ስወጣ ሰንደቅዓላማዬን ለልጄ ለማስረከብ ከዩኒቨርሲቲ አስወጥቼ ወደ ውትድርና አስገብቸዋለሁ"ይላሉ ኮሎኔል ደጀኔ ጸጋዬ ። 

ኮሎኔል ደጀኔ ጸጋዬ አሸባሪው ሕወሃት በሰሜን ዕዝ የደረሰው አሰቃቂ ጥቃት ተከትሎ በነበረው የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ በራያ ግንባር ለተሰለፈው የደቡብ ዕዝ የሰው ሃብት ልማትና ሚዲያ አስተባባሪ ነበሩ።

በወቅቱ ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ ሲያደርሱ የነበሩት ኮሎኔሉን የአሸባሪው ቡድን አፈ ቀላጤዎች ገድለናቸዋል ብለውም ፕሮፓጋንዳ ሰርተውባቸውም ነበር።

ኮሎኔል ደጀኔ አሁን ላይ ደግሞ የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ የጦር መኮንን ናቸው።

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጦር መኮንኑ፤ አገር ጠላት ሳይተናኮላት ታፍራና ተከብራ የምትኖርው ለአገር አጥር የሆነ ጠንካራ መከላከያ ሰራዊት ሲኖራት መሆኑን ገልጸዋል።

"መከላከያ ሰራዊት ከራሱ አልፎ ለሌሎች ሕይወት የሚሰራ፣ ለአጥንት፣ ደሙና ሕይወቱ የማይሳሳ፣ ራሱን ለህዝብ አሳልፎ የሚሰጥ ሰራዊት ነው" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ አንድ ልጃቸውን ከዩኒቨርሲቲ አስወጥተው ወደ ውትድርና በማስገባት ምሳሌ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከ30 ዓመታት በላይ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉት የጦር መኮንኑ፤ በ2008 ዓ.ም ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሲጀመር ስልጣን ላይ የነበረውን ሕወሃት ተወግዶ ለውጥ እንደሚመጣ ከጥቂት የጦር መኮንኖች ጋር እርግጠኞች ነበርን ይላሉ።

በዚህም አገራዊ ለውጥ ሲመጣ አገር ሕልውናዋ እንዳይናጋ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሲማር የነበረውን አንድ ልጃቸውን ከዩኒቨርሲቲ በማስወጣት ወደ መከላከያ ሠራዊት ማስገባታቸውን ይገልጻሉ።

ልጃቸው ዛሬ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ እያገለገለ የአስር አለቃ ማዕረግ አግኝቷል፤ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርቱን እየተማረ መሆኑንም ይናገራሉ።

"እኔ በቀጣይ ጡረታ ስወጣ ሰንደቅ ዓላማዬን ለልጄ አስረክባለሁ" ብለዋል።

"መከላከያ ሰራዊት የዕውቀት ማዕከል ነው፤ ከተራ ወታደር እስከ ጀኔራል የሚደረስበት፣ መሃንዲሶች፣ አየር አብራሪዎችና ሌሎች ተመራማሪዎች የሚፈሩበት የምርምር ተቋም ነው"ይላሉ ኮሎኔል ደጀኔ ጸጋዬ።

በመሆኑም ወጣቶች የአገር መከላከያ ሠራዊት የክብርና የበርካታ ሙያዎች ባለቤት የሚያደርግ ተቋም መሆኑን ተረድተው ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም