የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ያጓጓዛቸው የአደን መሣሪያዎች ሕጋዊ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ያጓጓዛቸው የአደን መሣሪያዎች ሕጋዊ ናቸው
ጳጉሜን 1/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ያጓጓዛቸው የአደን መሳሪያዎች አስፈላጊው የጉዞ ሰነድ ያላቸው ሕጋዊ መሣሪያዎች መሆናቸውን ገለጸ።
የአደን መሣሪያዎቹ መጓጓዝ ሕጋዊነትን የሚያረጋግጥ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተጻፈ ደብዳቤ መኖሩንም አየር መንገዱ ጠቁሟል።
በመሆኑም የሱዳን የዜና ወኪል ‘ሱና’ የአደን መሣሪያዎች በሱዳን መንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም ያለመ ነው የሚለው ዘገባ "ሐሰት" ነው ሲል አየር መንገዱ አስተባብሏል።
አየር መንገዱ መሣሪያዎቹ ለአደን አገልግሎት የሚውሉና አስፈላጊው የጉዞ ሰነድ ያላቸው ናቸው ብሏል።
የአደን መሣሪዎቹ አስፈላጊው የደኅንነት ማጣሪያ እስኪደረግላቸው ድረስ በአዲስ አበባ ለበርካታ ጊዜያት መቆየቱን ጠቅሷል።
ይህንንም ተከትሎ የአደን መሣሪያው ተቀባይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያዎችን እንዲልክ ወይንም 250 ሺህ ዶላር እንዲከፈለው በሱዳን ፍርድ ቤት አየር መንገዱን መክሰሱን አመላክቷል።
አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ደኅንነት ኃላፊዎች የማጣራት ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የአደን መሣሪያውን ለማጓጓዝ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ በሱዳን ለሚገኘው ተቀባይ ጦር መሳሪያውን ማጓጓዙን ገልጿል።