ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሞራል ስንቅ ሆኖኗል- የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችና አባላት

ጳጉሜን 1/2013 (ኢዜአ )  የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ግዳጃችንን በድል እንድንወጣ የሞራል ስንቅ ሆኖናል ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ተናገሩ።

መንግስት በትግራይ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች የመኸር እርሻቸውን ተረጋግተው እንዲያከናውኑና በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ  የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል።

ነገር ግን የህወሃት አሸባሪ ቡድን ይህን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ፈጽሟል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎችን  ጨፍጭፏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ የግለሰብና የመንግስት ንብረት ዘርፏል፣ ያልቻለውን ደግሞ አውድሟል።

በተጨማሪ ቤተ እምነቶችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ እጅግ አስነዋሪ ድርጊት ፈጽሟል።

የሽብር ቡድኑ እብሪትና ጭካኔ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣ በመቀስቀሱ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና መላው ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ብርቱ ክንዳቸውን እያሳረፉበት ይገኛሉ።

በወሎ ግንባር የሽብር ቡድኑን አይቀጡ ቅጣት አየቀጡ ያሉ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ለኢዜአ እንዳሉት፣ የህወሃት ሽብር ቡድን ወራሪ ሃይሎች በገቡበት ሁሉ ሽንፈትን እየቀመሱ ነው።

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠራዊቱ ጎን በመሆን ያበረከተው አስተዋጽኦ የላቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በገባባቸው አከባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ምሽግ ድረስ ስንቅ በማቀበል፣ መንገድ በመምራትና የመከላከያ ሠራዊቱ ደጀን በመሆን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ካላቸው ቀንሰው ለሠራዊቱ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን ለሠራዊቱ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ግዳጃቸውን በድል እንዲወጡ የሞራል ስንቅ እንደሆናቸው የተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ የሰው ሃይሉንና ትጥቁን እያዝረከረከ እየሸሸ መሆኑን ገልፀው፣ የህዝቡን ደጀንነት ይዘን የሽብር ቡድኑን ላይመለስ እንቀብረዋለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ለመከላከያ ሠራዊት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ብርጋዴር ጀነራል ሻምበል ፈረደ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠራዊቱ ያለውን ደጀንነት በተግባር በማሳየት የሠራዊቱ ብርታትና ጥንካሬ ምንጭ ሆኗል ብለዋል።

የሠራዊታችን ትልቁ አቅም ህዝባችን ነው ሲሉም ነው የተናገሩት።

በመሆኑም "ህዝቡን ደጀን አድርጎ የተነሳው የመከላከያ ሠራዊት ከልዩ ሃይል አባላትና ሚሊሻ ጋር በመተባበር ጠላትን በገባበት ቦታ ሁሉ እየደመሰሰ ይገኛል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም