ቀጥታ፡

"የኢትዮጵያዊነት ቀን" ከኢትዮጵያ መገለጫዎች በጥቂቱ

አዲስ አበባ (ኢዜአ)  ጷግሜ 1/2013  ጳጉሜን 1 "የኢትዮጵያዊነት ቀን" ኢትዮጵያዊነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መገለጫዎች የሚባሉ የተለያዩ ነጥቦች ተብራርተዋል።

- ቀደምትነት

የሰው ልጅ መገኛ፣ የቡና መገኛ፣ የአባይ መገኛ፣ በአገረ መንግስት ምስረታ የቆየና የካበተ ታሪክ እና ሌሎችም ተጠቅሰዋል።

- የእውነትና የእምነት አገር ኢትዮጵያ

በክርስትና እና አስልምና ሃይማኖት ጥልቅ ታሪካዊ ትንታኔ የሚሰጥባት አገር መሆኗ ተነስቷል።

- ህብረ ብሄራዊነት

ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋ፣ ባህልና ማንነት መገለጫዎች ያላት የተለየች አገር ስትሆን የጋራ የሆኑ የሚያስተሳስሯቸው እሴቶች ያላቸው ናቸው።

- የሰላምና ፍቅር አገር ኢትዮጵያ

በታሪኳ ማንንም አገር ገፍታ የማታውቅ፤ በእስያ ከኮሪያ እስከ አፍሪካ በሰላም ማስከበር ዘመቻ በቀዳሚነት የተሳተፈችና ውጤት ያስመዘገበች አገር ናት።

ለዘመናት የራሷ መንግስት ያላትና ወራሪን በመመከት ታላቅ ታሪክ የተመዘገበባት መሆን ይጠቀሳል።

- ጀግንነት

የኢትዮጵያዊያንን ጀግንነት የትኛውም የዓለም አገር የሚያውቀውና በጀግንነት የሚፋለሙ መሆናቸውን ይረዳል።

የውጭ ወራሪን በመመከት የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነች የታላቅ ታሪክ ባለቤት መሆኗ የአደባባይ ሃቅ ነው።

- ኩራትና ክብር

ኩራትና ክብር የኢትዮጵያዊያን ልዩ መገለጫ ሆኖ ይገኛል። በማንነቱ የሚኮራና በአንድነቱ የሚመካ ህዝብ ለጠላትና እብሪተኛ የማይንበረከክ መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው።

- ዘላለማዊነት

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ከጥንት ጀምሮ ዘላለማዊ ሆና የኖረችና እየኖረች ያለች አገር መሆኗ። ኢትዮጵያ እነዚህና ሌሎችም ጥልቅ መገለጫዎች ያሏት አገር መሆኗ በምሁራኑ እየተዘከረ ይገኛል።

የኢትዮጵያዊነት ቀን በተለያዩ መርሃ ግብሮች በዛሬው እለት እየተዘከረ ሲሆን፤ በነገው እለትም ጳጉሜን 2 "የአገልጋይነት ቀን" በተለያዩ መርሃ ግብሮች የሚታሰብ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም