"አሸባሪው ህወሃት በህይወት ዘመኑ ለማፈራረስ የደከመባትን ኢትዮጵያ በሞቱ አንድነቷን አጠናክሯል" - ኢዜአ አማርኛ
"አሸባሪው ህወሃት በህይወት ዘመኑ ለማፈራረስ የደከመባትን ኢትዮጵያ በሞቱ አንድነቷን አጠናክሯል"
ጳጉሜን 1/2013 (ኢዜአ) "አሸባሪው ህወሃት በህይወት ዘመኑ ለማፈራረስ የደከመባትን ኢትዮጵያ በሞቱ አንድነቷን አጠናክሯል" ሲሉ የወሎ ግንባር የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ ተናገሩ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት የቡድኑን የመጨረሻ የአገር ክህደት ያሳየ ነበር።
በዚህን ጊዜ አገር ሲነካ የማይታገሰው የኢትዮጵያ ህዝብ በአሸባሪው ድርጊት ቁጣው ተቀሰቀሰ።
ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነሳት አሸባሪ ቡድኑን ወደ ዋሻ ቢመለስውም መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ዳግም በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ፈፅሟል።
አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ያልፈፀመው ግፍ፣ በደልና ሴራ እንዳልነበር ግልፅ ቢሆንም አንገቱን ወደ ሞት ጉድጓድ ማስገባት የጀመረው በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈፅም መሆኑን የወሎ ግንባር የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ ገልጸዋል።
በመሆኑም "ወያኔ በህይወት ዘመኑ ያበላሻትን ኢትዮጵያ አሁን እየሞተ አንድነቷን አጠናክሯል" ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ህዝብ ለማደናገር ቢሞክርም በየአካባቢው ተመክቶ ግብአተ መሬቱ እየተፈፀመ ይገኛልም ነው ያሉት።
አሸባሪው ሰርጎ በገባባቸው አማራና አፋር ክልሎች ያደረሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና የሽብር ተግባር የቡድኑን የጭካኔ ጥግ ያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ በቡድኑ አፈ ቀላጤ ጌታቸው ረዳ በኩል "ደሴን የተወናት ለህዝቡ አዝነን ነው" በሚል "እየሞትኩኝ አይደለም በማለት እራሱን እየዋሸ ይገኛል" ብለዋል አቶ ወንዳለ።
አሸባሪው ህወሃት ሰርጎ በገባባቸው የወሎ አካባቢዎች ቤተክርስቲያን አውድሞ፤ መድረሳ ላይ የነበሩ ሙስሊሞችን ረሽኖ፣ ወጣቶችን በአደባባይ መግደልና ሌሎችንም በደሎችን ፈፅሟል ብለዋል።
በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ባደረገባቸው አካባቢዎች ህዝቡን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ አደናግሮ እንደነበር አስታውሰው፣ በሂደት የቡድኑን ጭካኔ በተግባር በመመልከት ህዝቡ ተፋልሞታል ነው ያሉት።
የወሎ ህዝብ የሽብር ቡድኑን በገባበት እየገባ እየቀበረው ይገኛልም ብለዋል።
በተለይም የወሎ አርሶ አደሮች አሸባሪውን በመቅጣት "ለፍቅር ካልሆነ ለጠብ የማይመቹ" መሆናቸውን በአስደናቂ ጀግንነት ታጅበው አሸባሪውን ደምስሰዋል ነው ያሉት።