ቀጥታ፡

የህወሃት ወራሪ ሃይል ለሃገር ዳግም ስጋት እንዳይሆን እየተሰራ ነው-አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ደሴ ጳጉሜን 1/2013 (ኢዜአ ) ''የህውሃት ወራሪ ሀይል ዳግም የአገሪቱ ስጋት በማይሆን መልኩ በጋራ መከላከልና ህልውናን ማስቀጠል የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኖ እየተከናወነ ነው'' ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታወቁ።

በደሴ ከተማ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ምክክር እየተደረገ ነው።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክክር መድረኩ ላይ እንደተናገሩት አሸባሪው ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር ወግኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ነው።

ህወሀት ወራሪ ሃይሉን በአማራና አፋር ክልሎች በማሰማራት በሕዝብ ላይ በደል እየፈፀመ መሆኑን ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ጠብቆ ወራሪ ሃይሉ ለአገርና ህዝብ ዳግም ስጋት በማይሆንበት መንገድ  በመደምሰስ ህልውናውን የሚያስቀጥልበት ወቅት ነው" ብለዋል።

ወጣቱ በየአካባቢው ተደራጅቶና ሰልጥኖ የአገሪቱን ነፃነትና ሉአላዊነት በማስቀጠል ግዴታውን እንዲወጣ አቶ ገዱ አሳስበዋል።

መንግሥት ሕዝቡንና የጸጥታ ሃይሎችን በማስተባበር አሸባሪው በድን የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ጥፋት ለመመከት በተደራጀ አግባብ እየሰራ መሆኑን አቶ ገዱ አብራርተዋል።

በውይይቱ የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የደሴ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም