ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸነፊ ሆኑ

ነሐሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የመንግስታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

የ2013 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት በአስር ዘርፎች ከ500 በላይ ዕጩዎች ተጠቁመው፤ ከእነዚህ መካከል 30 ሰዎች የመጨረሻ ዕጩ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

በዛሬው ዕለትም በአስር ዘርፎች ለመጨረሻ ዕጩ ከቀረቡት ሶስት ሶስት ዕጩዎች ውስጥ የመጨረሻ አሸናፊዎች ይፋ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የመንግስታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት የመወጣት ዘርፍ የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማትን አሸንፈዋል።

በመምህርነት ዘርፍ ዶክተር ልዑልሰገድ አለማየሁ፤ በበጎ አድራጎት ዘርፍ አቶ አማረ አስፋው፣ በቅርስና ባህል ጥበቃ ዘርፍ ቢላል ሃበሽ የማህበረሰብ ሙዚየም ማዕከል፣ በሳይንስ ዘርፍ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተፈራ፣ የማህበራዊ ጥናት ዘርፍ ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ በንግድና ስራ ፈጠራ ዘርፍ አቶ በላይነህ ክንዴ አሸንፈዋል።

በተጨማሪም የ2013 የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚም ይፋ ይደረጋል። 

የበጎ ሰው ሽልማት በኢትዮጵያ በጎ የሰሩ እና ለሌሎች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ማበረታታት እና እውቅና ለመስጠት ዋና ዓላማ አድርጎ በየዓመቱ የሚካሄድ ሽልማት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም