የደቡብና ጋምቤላ ክልሎች በሠላም፣ ልማትና ፀጥታ ዙሪያ የጋራ ምክክር ጀመሩ

50

ሚዛን አማን፣ ነሀሴ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የደቡብና ጋምቤላ ክልሎች አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች በሠላም፣ ልማትና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በሚዛን አማን ከተማ የጋራ ምክክር ጀመሩ።

በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በተጀመረው ውይይት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑመድ ኡጁሉ ተገኝተዋል።

አቶ ርስቱ ይርዳው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሁለቱ ክልሎች ጠንካራ ባህላዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር አላቸው።

"ክልሎቹ ሰፊ ለም መሬት፣ በተፈጥሮ ሀብትና ዝናብ የታደሉ ቢሆኑም ህዝቡ ሀብቶቹን በአግባቡ እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ በችግር ውስጥ ቆይተዋል" ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ስልጣን ላይ እያለ ክልሎቹ ሀብታቸውን በማልማት እንዲጠቀሙ ከማድረግ ይልቅ ክልሎቹን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ሴራ በፀጥታ ኃይሉ ጠንካራ እንቅስቃሴና በህዝቡ ተሳትፎ እየከሸፈ መሆኑን ገልጸው፤ “ልማትን ወደፊት የማስቀጠል ተግባር ላይ እንገኛለን" ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዑመድ ኡጁሉ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተለይ የጋምቤላ ክልል ህዝብ ልማት ተነፍጎት ሀብቱ ሲዘረፍ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ ልማትን በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ "መድረኩም ሁለቱ ክልሎች በጋራ አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ ያግዛል" ብለዋል።

ቀጠናው ለፀጥታ ችግር ተጋላጭ መሆኑን ገልጸው፤ በምክክር መድረኩ ለችጎሮቹ የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተናግረዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን "ጊዜው ያለውን ሀብት በማልማት ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ የምናፋጥንበት ነው" ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክልሎቹ ርዕሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከአምስት አጎራባች ዞኖችና አሥር ወረዳዎች የተወጣጡና በየደረጃው ያሉ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም