የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ማስቀጠል በሚችል መልኩ እንደሚካሄድ ተገለጸ

86
መቀሌ ነሀሴ 7/2010 የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ /ህወሓት/ 13ኛው ጉባኤ  የተጀመረው የለውጥ ሂደት ወደፊት ሊያራምድ በሚችል መልኩ እንደሚካሄድ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ፡፡ የድርጅቱ  ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በህወሓት 13ኛው ጉባኤና በወቅታዊ ጉዳዮች  ዙሪያ ትናንት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው  እንዳሉት የህወሓት 13ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በቅርቡ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ከዚህ ቀደም ያካሄዳቸው ጉባኤዎች የየራሳቸው የታሪክ ምዕራፍ የነበረባቸው ናቸው፡፡ በቅርቡ የሚያካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤ  አሁን ካለው ችግር የሚያወጣና በቀጣይ በሁሉም መስኮች  ፈጣን ለውጦች ለማምጣት በሚችል መልኩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ "ጉባኤው  በክልሉና በሀገሪቱ  እየተካሄዱ ባሉት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የነበሩት ክፍተቶች  በሚዳስስ መልኩ ትኩረት ይሰጥበታል "ብለዋል። ዶክተር ደብረጽዮን እንዳመለከቱት  በሀገሪቱ የተጀመረው የፀረ ድህነት ተጋድሎ ለማጠናከርና ወደ መካከለኛ ገቢ ለመግባት የያዘችው ራዕይ በፍጥነት ለማሳካት በሚደረገው ጥረቶችና  ተግዳሮቶች የድርጅቱ ሚናም ይዳሰሳል። ድርጅቱ በክልሉ ያለው የመሪነት ሚና ለማጠናከር እንዲሁም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እንዲቻል ብቃትን መሰረት ያደረገ የአመራር መተካካት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል። የለውጥ ጉዞውን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶች ወደ አመራሩ የማስገባቱ ስራ በጉባኤው ትኩረት እንደሚሰጠውም የድርጅቱ ሊቀመንበር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም