ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለመታደግ የሚደረገውን ትግል በመደገፍ የቁርጥ ቀን መከታ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለመታደግ የሚደረገውን ትግል በመደገፍ የቁርጥ ቀን መከታ ሆነዋል
ነሐሴ 29/2013 (ኢዜአ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት መንግሥት ኢትዮጵያን ለመታደግ እያካሄደ ያለውን ትግል በመደገፍ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን እያስመሰከሩ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።
መንግሥት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የያዘውን ቁርጠኝነት እንደሚደግፉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታውቀዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የሉዓላዊነት አደጋ ለመመከት ዓላማ ያደረገ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሂደዋል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው ምክክርም የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ን ጨምሮ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ እና ሌሎች የፖርቲ አመራር አባላት ታድመዋል።
በመድረኩ "በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች እና የመንግሥት ሚና ምን ይመስላል?" በሚል የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሚኒስትሩ ዛዲግ አብርሃ እና የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል።
አሸባሪው ህወሓት ከበኩር ልጁ ሸኔ ጋር ጥምረት በመፍጠር "እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ" በሚል ከንቱ ቅዠት ጦርነት መክፈቱ ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ፣ የዲፕሎማሲ ጫና ጨምሮ የውጭ ጠላትና የውስጥ ባንዳዎች ዓይነት ብዙ ጦርነት መክፈታቸው ተገልጿል።
ይህንን ዓይነት ብዙ ጦርነት በመመከት የአገርን ሉዓላዊነት ለመታደግም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ "የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጽኑ አንድነት ይጠይቃል" ተብሏል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር እና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ውይይቱ የአገር ሉዓላዊነትን ለመታደግ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።
የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት ኢትዮጵያን ለመታደግ የያዘውን ተጋድሎ በመደገፍ የአገራቸው የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን በይፋ እያስመሰከሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአገርን ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት የገንዘብ፣ የደምና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመለገስ አጋርነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ፤ እስካሁንም ኢትዮጵያ ጸንታ የቆመችው ፈተና ስላልገጠማት ሳይሆን ያጋጠሟትን ፈተና ሁሉ በጀግኖች ልጆቿ ጽናት መመከት በመቻሏ እንደሆነ አስታውሰዋል።
የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅም ገዥ፤ ተፎካካሪ ፓርቲ ሳይባል ሁሉም የሚችለውን አስተዋጽኦ በማበርከት የጠላትን ህልም ማምከን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አሸባሪው ህወሃት አገርን ለማፍረስ ከያዘው እብደት በስተጀርባ ሌሎች ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የማይፈልጉ ጠላቶች መኖራቸውን መረዳት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በተለይም አሸባሪው ህወሃት በሚነዛው ፕሮፓጋንዳ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አንደሚያሳስት ጠቁመው፤ እነሱም በሀሰት መረጃ ላይ ተንተርሰው የተደራደሩ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ በበኩላቸው፤ ይህ ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ ከመጻፍ ተሸጋግሮ ታሪክ የመስራትና ማስመዝገብ የሚችልበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
አገር ያለችበትን ሁኔታ በመረዳትም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጎን በመቆም ኢትዮጵያን ለመታደግ እየተዋደቀ ከሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ጎን መሰለፋቸውን ተናግረዋል።
ውይይቱ ተሳትፎ ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉት፤ የድርጅት ወይም የፓርቲ አላማን ለይደር በመተው አገርን ለማዳን የምንዘጋጅበት ወቅት አሁን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲ ማንኛውንም የፖለቲካ ልዩነት ወደ ጎን ትቶ ቅድሚያ ለአገር ሉዓላዊነት መጠበቅ ከመንግሥት ጎን መቆም እንደሚገባው አንስተዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን እንደ ሸኔ እና ሌሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመገዳደር የሚሹ የጥፋት ኃይሎችን ለመመከትም ከመንግሥት ጋር በመሰለፍ የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በቀጣይም አገር ወደ ቀደመ ክብርና ማንነቷ ተመልሶ ህዝቦቿ የሰላም አየር እስኪተነፍሱ ድረስ መንግሥት የያዘውን የህልውና ተጋድሎ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
ፓርቲዎቹ አሸባሪው የህወሓት ቡድንን ለመደምሰስ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ በማስቀጠል ቡድኑ እየነዛ ያለውን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች መመከት እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል።
ከምክክር መድረኩ በኋላም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ የያዘችውን ዓላማ እንደሚደግፉ በጋራ የአቋም መግለጫቸው አረጋግጠዋል።