የምክር ቤቱ ተቋማዊ ለውጥ ትብብርን መሰረት ያደረገ የመንግሥታት ግንኙነት እንዲጠናከር ጉልህ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የምክር ቤቱ ተቋማዊ ለውጥ ትብብርን መሰረት ያደረገ የመንግሥታት ግንኙነት እንዲጠናከር ጉልህ ሚና አለው
ነሀሴ 29/2013 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተቋማዊ ለውጥ የመንግሥታትን ግንኙነት ጤናማና ትብብርን መሰረት ያደረገ እንዲሆን በማስቻል ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።
ምክር ቤቱ የተሰጠውን ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚያስችለውን ተቋማዊ ለውጥ /ሪፎርም/ ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል።
የለውጥ ሥራውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል።
ምክር ቤቱ ዛሬ በጥናቱ ላይ ለተሳተፉ ተቋማትና ባለሙያዎች እውቅና ሰጥቷል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ እንደገለጹት፤ ተቋማዊ ለውጡ ምክር ቤቱን በአደረጃጀት፣ በአሠራርና በሰው ኃይል እንዲጠናከርና ውጤታማ ሙያዊና አስተዳደራዊ ድጋፍ እንዲሰጥ የሚያስችለው በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነው።
ሕገ-መንግሥቱን በትክክል ለመተርጎምና የሕግ-የበላይነት ለማረጋገጥ ከማገዝ ባሻገር የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ለማስከበርም ሪፎርሙ ጉልህ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
ለብሔረ መንግሥት ግንባታ፣ ለሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት መጎልበት እንዲሁም ትብብርን መሰረት ያደረገ የመንግሥታትን ግንኙነት ለማጠናከርም ከፍያለ አስተዋፅኦ እንዳለው አክለዋል።
ለፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ ለዳበረ ዴሞክራሲ መስፈን፣ ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥና ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም በመገንባትም እንዲሁ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ዋናዎቹ የእውቀት ሥፍራ እንደመሆናቸው መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት በለውጥ አሰራር ሂደት የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው ብለዋል።
ከመማር ማስተማር ተግባራቸው ባሻገር እውቀታቸውን ማስፋፋት እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም /ዩ.ኤን.ዲ.ፒ/ ተወካይ አቶ ሽመልስ አሰፋ ማንኛቸውም ፖሊሲዎች ከስሜታዊነትና ከርዕዮተ ዓለም ተጽዕኖ የራቁና በጥናት ላይ የተመሰረቱ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች እንዲረጋገጡ ጥናቶችን መሰረት ያደረጉ ሆነው መሰራት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የምክር ቤቱን ሥልጣንና ተግባራት ለመዘርዘር የወጣውን አዋጅ የማሻሻል፣ የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓትን ለመደንገግ የወጣውን እንዲሁም የፌዴራል ድጎማ እና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል አሠራር ሥርዓትን ለመወሰን የወጡ አዋጆችን የማሻሻል ሥራ መሰራቱ ተገልጿል።