ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃትን ለመደምሰስ ወጣቶች ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በአውደ ውጊያው መሰለፋቸውን እንዲቀጥሉ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃትን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ ወጣቶች ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሰለፋቸውን እንዲቀጥሉ  በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የህዝብ ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ ጥሪ አቀረቡ።

"አማራ ለአገር ደጀን ትሆን ዘንድ የመከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቀል" በሚል መሪ ሀሳብ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በምክትል ርዕሰ - መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የህዝብ ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ በወቅቱ እንዳሉት፤ የአሸባሪው ህወሓት በእኩይ ተግባሩ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ወደ አማራ ክልል ገብቷል።

አሸባሪው ቡድኑ አማራ ክልል በመግባት ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰው፤ አብዛኛውን ሰርጎ የገባው ኃይል በደረሰበት አጸፋዊ እርምጃ መደምሰሱን ነው የገለጹት።

አሸባሪው ሕወሃት በአማራ ክልል እየፈጸመ ያለው ጥቃት እየተመከተና አጸፋዊ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን ቡድን እስከመጨረሻ በመደምሰስ አስተሳሰቡን ጭምር መቅበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም ወጣቶች በአንድነት በአውደ ውጊያው ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብ የጥቁር ህዝቦች ድል ምሳሌ ነው” ያሉት ደግሞ ባለሃብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ፤ የቀድሞ አባቶቻችንን ታሪክ ከማውራት ባለፈ በአሁኑ ትውልድ ዳግም ታላቅ ገድል መፈጸም እንደሚገባ አብራርተዋል።

“እኛ ወጣቶች ጦርነትን በባዶ እጁ፤ ኦሊምፒክን በባዶ እግሩ ድል ያደረጉ ተአምረኛ ህዝብ ልጆች ነን” የሚል መፈክርን ያነገቡ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው፤ አሸባሪውን ቡድን ለመፋለም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። እነዚሁ ወጣቶቹ በአገር ህልውናላይ የመጣውን ጠላት ለመደምሰስ በወኔ ተነስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም