ሕዝቡ፣ መከላከያ ሠራዊቱና የፀጥታ ኃይሎች አሸባሪውን ህወሓት አይቀጡ ቅጣት እየቀጡት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝቡ፣ መከላከያ ሠራዊቱና የፀጥታ ኃይሎች አሸባሪውን ህወሓት አይቀጡ ቅጣት እየቀጡት ነው
ነሀሴ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የጥፋት ሃይሉን ትህነግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱን ለመፈፀም ሕዝቡ፣ መከላከያ ሠራዊቱና የክልሎች የፀጥታ ኃይሎች ብርቱ ክንዳቸውን እያሳረፉበት ነው ሲሉ የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው የትሕነግ የጥፋት ኃይል አፈር ልሶ እንዳይነሳ ለመፋለም እምነታችን የፀና ነው ብለዋል ኮሎኔሉ።
ኮሎኔሉ ይህን ያሉት ማዕከሉ ምልምል ወታደሮች፣ የዕዙን የ27ኛ ክፍለ ጦር እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስ የቡድን መሳሪያ ሰልጣኞች ወታደራዊና የፖሊስ መኮንኖች በተገኙበት ዛሬ ሲያስመርቅ ነው።
ኮሎኔል ደጄኔ የጥፋት ሃይሉን ለአንዴና ለመጨረሻ ለመደምሰስ ከየክልሉ የተውጣጡ ሰልጣኞች መሰረታዊ የአካል፣ የቴክኒክና የስነ-ልቦና ስልጠናቸውን በወኔና በብቃት በማጠናቀቃቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን ላለፉት 45 ዓመታት ፀረ ሕዝብና ኢትዮጵያ ጠል በመሆኑ ራሱን በራሱ እየበላ ያደገ ቡድን መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ የሽብር ቡድን ዳግም ላይመለስ ይቀበራልም ነው ያሉት።
የጥፋት ቡድኑ ላለፉት 27 ዓመታት በስልጣን ላይ እያለ ለጥቂት ቡድኖች ጥቅም በኢትዮጵያዊያን ላይ ያልፈፀመው ግፍና መከራ እንደሌለ አስታውሰው፤ ይባስ ብሎ ቀይ መስመር በማለፍ የአገር መከታ የሆነውን የሰሜን ዕዝ በክህደት አረመኔያዊ ጥቃት ፈፅሞበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን የጥፋት ኃይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱን ለመፈፀም ሕዝቡ፣ መከላከያ ሠራዊቱና የክልሎች የፀጥታ ኃይሎች ብርቱ ክንዳቸውን እያሳረፉበት መሆኑን ገልጸዋል።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን የጦርነት ዘይቤና ባደፈ አስተሳሰብ እየተመራ እንደ አንበጣ የመጣውን አሸባሪ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያዊያን አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ጀምረዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ምሩቃኑ ይህ የጥፋት ኃይል ዳግም አፈር ልሶ እንዳይነሳ እስኪጠፋ በመፋለም ድል እንደምትቀዳጁ እምነታችን የፀና ነው ብለዋል ኮሎኔሉ።
የታሪካዊ ድል ባለቤት አካል በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል ያሉት ኮሎኔል ደጀኔ፤ ሰልጣኞች ያገኙትን የንድፈ ሀሳብና የተግባር ዕውቀት በመጠቀም አሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ በአገር ሕልውና ዘመቻው ስኬታማ ግዳጅ እንደምታከናውኑ እምነት አለኝ ብለዋል።