በቻይና የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቋመ
አዲስ አበባ ነሀሴ 7/2010 በቻይና የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቋመ። “ለሰላምና ለአንድነት በፍቅር መደመር” በሚል መሪ ቃል በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነሐሴ 5 ቀን 2010 ዓ.ም የመደመር ቀን ተከብሯል። በስነ-ስርዓቱ ላይ በቤጂንግ የሚገኙ የዲያስፖራ አባላት፣ በተለያዩ የቤጂንግ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የኤምባሲው ሰራተኞች ተሳትፈዋል። ቀኑ በተከበረበት ወቅት በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስተባብር የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። አስተባባሪ ኮሚቴው አራት አባላት እንዳሉትም ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው። በቀን አንድ የአሜሪካ ዶላር በመለገስ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀው ነበር። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንን ተሳትፎ ለማቀናጀትና የልገሳውን ገንዘብ ለማሰባሰብ፥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በሚል ስም የሂሳብ ቁጥር መከፈቱም ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድን የሚያማክር ምክር ቤት በማቋቋም ምክር ቤቱን የሚያማክሩ 15 አባላትን ሰይመዋል።