ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ የመግባቢያ ውይይት በአዲስ አበባ ሊካሔድ ነው

አዲስ አበባ ነሀሴ 7/2010 የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ መግባባትና የዕርቀ-ሰላም ውይይት በአዲስ አበባ ሊካሔድ ነው። የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባትና እርቀ-ሰላም ዓለምአቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ የፊታችን ሐሙስ የሚካሄደውን ውይይት አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የአስተባባሪው ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር በዛብህ ደምሴ እንደገለጹት ውይይቱ በወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ በጋራ መምከርን ዒላማው አድርጓል። ውይይቱ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ለማስፋት፣ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት ጥምረት ለመመስረት በር የሚከፍትና አንድነት ለመጠናከርም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። ኢሕአዴግን ጨምሮ  የተለያየ አመለካከት ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን የሃይማኖት ድርጅቶች ተወካዮች፣ የሲቪክ ማህበራትና ሌሎችም በውይይት መድረኩ መሳተፍ የሚፈልጉ አካላት እንደሚገኙም ተናግረዋል። በህገ-መንግስት ጉዳዮች ላይ በፓርቲዎች የጋራ መግባባት መፍጠር፣ የተለያየ የፖለቲካ አመለካካት ባላቸው ሰዎች ከዚህ ቀደም የተወሰዱ እርምጃዎችና በአገር ላይ ያስከተሉት ችግሮች በውይይቱ ይዳሰሳሉ። ከተሳታፊዎችም ጤናማና አገርን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚችል አስተያየት የሚጠበቅ ሲሆን ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ሃሳብ ከኮሚቴው እንደሚቀርብ ሰብሳቢው ተናግረዋል። የውይይት መድረኩ የተሳካ እንዲሆን መንግስት ድጋፍ እንዲያደረግ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል። ኮሚቴው በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በአሜሪካ በተካሄደው የመጀመሪያ ውይይት ከ26 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተው ኮሚቴ መመስረታቸው ይታወቃል። በዚህም በአገር ውስጥ  የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እና የኦሞ ሕዝብ ድርጅት ኮሚቴውን ወክለዋል። ከውጭ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተወጣጡ ስድስት የተፎካካር ፓርቲዎች ኮሚቴውን መወከላቸውን ጠቁመዋል። በአገር ቤት ብቻ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ 62 የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚገኙ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም