መንግስት ስርዓት አልበኝነትን ማስቆም አለበት-የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ስርዓት አልበኝነትን ማስቆም አለበት-የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲስ አበባ ነሀሴ 7/2010 በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ግጭቶች የባሰ ስጋት ሳያመጡ መንግስት ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጥሪ አቀረበ። አገሪቱ ለውጦች እያስተናገደች ብትሆንም በዛው ልክ በየቦታው እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ስጋት እየሆኑ ነው። የኃይማኖት አባቶች ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተገኝተው በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል። በቅርቡ በባሌ፣ በጣና በለስ፣ በጎዴ፣ በድሬደዋ ጅግጅጋ፣ በሻሸመኔና በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠረ ሁከትና አደጋ የንፁሃን ህይወት አልፏል፤ የንብረት ውድመትም ደርሷል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ በዚሁ ወቅት ድርጊቱ ሊፀየፉትና ህግ ባለበት አገር ሊከናወን የማይገባ ተግባር ነው ሲሉ አውግዘዋል። ይህ ድርጊት እንዲቆም መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበትም ብለዋል። የሃይማኖት አባቶቹ እንዳሉት አገሪቱ የሰላም ምድር ብትሆንም አሁን ግን ሰላሟን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ተግባራት እዚህም እዚያም እየተስተዋሉ ነው። ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለው አንድ አገር በመሆኑ ተስማምቶና ተከባብሮ መኖር ያስፈልጋል ሲሉም ነው የገለፁት። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እድሪስ በበኩላቸው በእስልምና ኃይማኖት የክርስትና እምነት ይጥፋ የተባለበት አስተምህሮ አለመኖሩን በመግለፅ በሱማሌ የደረሰውን የሰውና የንብረት ጥፋት አውግዘዋል። በአጠቃላይም በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሰው ልጅን የከበረ ህይወት ማጥፋት ተግባር ወደፊት ለባሰ መጠፋፋት ምክንያት በመሆኑ መንግስት ከምክር ያለፈ አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል። በማህበራዊ መስተጋብር አብሮ የመኖር ታሪክ ያለውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ በዘርና በኃይማኖት በመከፋፈል አገሪቱን አደጋ ላይ መጣል የለበትም ብለዋል። ዛሬ በአንዱ ዘርና ኃይማኖት ላይ የተጀመረው ነገ በሌላው የማይደገምበት ምክንያት ባለመኖሩ መንግስት ቀድሞ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መስራት አለበት ብለዋል። ለጥቁር ህዝቦች ምሳሌ የሆነች አገር ዛሬ ታሪኳን መቀየር የለባትም ያሉት ደግሞ የካቶሊክ ካርዲናል ብርሃነ-ኢየሱን ናቸው። ዴሞክራሲን ለማስፋት በተከፈተው መንገድ የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ ስርዓት አልበኝነትና ህገ-ወጥነት እየተባባሰ መምጣቱንም ገልፀዋል። ሰው በፈለገ ሰዓት ተነስቶ ካንዱ ክልል ወደሌላ ይሄድ ነበር ዛሬ ግን እንቅስቃሴው እንዲገደብ እየሆነ ነው ብለዋል። መንግስት ዜጎችን ከስጋት ለማዳንና ሰላም ለማስጠበቅ ጥሪ እስኪደረግለት መጠበቅ የለበትም ነው ያሉት። በሶማሌ የታየው ጥፋት በኃይማኖት የተቀሰቀሰ ግጭት አይቆምም በማለት ታቅዶ በግለሰቦች የተከናወነ ነው ሲሉ ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ ተናግረዋል። "ወጣቱ የተፈቀደውን የዴሞክራሲ ስጦታ መሸከም ባለመቻሉ ትልቅ ጥፋት እየተካሄደ ነው" ብለዋል። መንግስት ይህን በቶሎ ማስተካከል ካልቻለ በሌሎች አገራት የሚታዩ ቀውሶች ውስጥ እኛም እንድንገባ ያደርገናል ነው ያሉት። በሶማሌና በሌሎች ክልሎች ትናንት ደግሞ በሻሸመኔ የታየው ድርጊት የዚህ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሲከናወኑ ያወገዝናቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ዛሬ እኛ መፈፀም የለብንም በማለት የኃይማኖት አባቶች ምክራቸውን አስተላልፈዋል። የተጀመረውን ለውጥ ለማገዝ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለውጡን ውጤታማ ማድረግ ካልተቻለ ወጣቱ ነገ የሚኖርበት፤ ቤተሰብ መስርቶ ልጅ የሚወልድባት አገር ስጋት ውስጥ እንደምትገባ ጠቁመዋል። ወጣቱ የልማት ኃይል ቢሆንም በዛው ልክ የጥፋትም ኃይል ይሆናልና መንግስት ወጣቱን በህጋዊ መንገድ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ማስተካከል ይገባዋል ብለዋል። በመጨረሻም የኃይማኖት አባቶቹ ሰሞኑን በሶማሌ ክልል በተፈጠረው ጥፋት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን ወገኖች ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም በየተቋሞቻቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።