ፌዴራል ፖሊስ የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ አባላትን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ፌዴራል ፖሊስ የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ አባላትን አስመረቀ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ በደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ አባላቱን ዛሬ አስመርቋል።
አባላቱ የቡድን መሳሪያዎች በሆኑት በስናይፐር፣ በመትረየስ፣ በድሽቃ እና አር.ፒ.ጂ /ፀረ ታንክ ላውንቸር/መሳሪያዎች ነው የሰለጠኑት።
በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ኢትዮጵያ ለወራሪ ጠላት ያልተንበረከከች ናት፤ የነፃነት ተምሣሌት እንድትሆንም አያቶቻችን ከሙሉ ታሪኳ ጋር አስረከበውናል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ 'የመከላከያ ሠራዊት ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነትና ወኔ ኢትዮጵያ እንዳትደፈርና በልጆቿ ተከብራ እንድትቀጥል አድርጓል' ሲሉ ተናግረዋል።
ከጠላት ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመበተን ጦርነት ያወጀውን የህወሓት የሽብር ቡድን የዚህ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ ለመደምሰስ መስራት ትልቅ ኩራት መሆኑን ገልፀዋል።
አሸባሪው ቡድን ሕፃናትን ለጦርነት በመማገድ የትግራይ እናቶችን እያስለቀሰ፤ በወረራቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎችም ሴቶችን፣ ህፃናትና አረጋዊያንን በጭካኔ እየገደለ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ አረመኔ አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች በተቀናጀ አግባብ እየሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተመሳሳይ ዛሬ ለምረቃ የበቁት የደቡብ ዕዝ ምልምል ወታደሮችና የከባድ መሳሪያ ሰልጣኝ የሠራዊት አባላት 'ዕውቀታችሁን በመጠቀም የሚሰጣችሁን ግዳጅ በመውሰድ ጠላትን መቅጣት ይገባችኋል' ብለዋል።
ኢትዮጵያ የመልማትና የማደግ መብት አላት፣ ማንም ሊያዛት አይችልም፣ ተላላኪ መንግስትም አይፈጠርም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ አሸባሪው ቡድን ከውጭ ኀይሎች ጋር በመላላክ አገር ለማሸበር ቢጥርም አልተሳካለትም ነው ያሉት።
"ተመራቂ የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ ፖሊሶች በምትሄዱበት ሁሉ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት በሰለጠናችሁበት ዕውቀትና ክህሎት የኢትዮጵያ ነፃነት እንዲቀጥል መስራት ይገባችኋል" ብለዋል።
ለአባላቱ ስልጠና የሰጠውን የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከልም አመስግነዋል።
የከባድ መሳሪያ ምድብተኛ የፖሊስ አባላቱ መመረቅ ፖሊስ በሕልውና ዘመቻው እያደረገ ያለውን ተጋድሎ አቅም የሚያጎለብት መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም የፖሊስ ተቋም የጀመረውን ሪፎርም በማዘመን በሕልውና ዘመቻ ተልዕኮውን ለመፈፀም ብሎም ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።