አሸባሪዎቹ ከኢትዮጵያ እስከሚወገዱ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን

79

አርባ ምንጭ፣ ነሐሴ 29/2013 (ኢዜአ) አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ከኢትዮጵያ ተወግደው ህዝቡ አስተማማኝ ሰላም እስኪያገኝ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የጋሞ ዞን ምክር ቤት ምከትል አፈ ጉባዔ አስታወቁ።

የጋሞ ዞን ምክር ቤት  15ኛ መደበኛ ጉባዔውን በአርባ ምንጭ ከተማ እያካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔዋ ወይዘሮ መሰረት ማዶሌ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ፤  ሀገራችን ከገጠማት ፈተና መውጣት የምትችለው በዋናነት በህዝቧ አንድነትና ትብብር ብቻ ነው ብለዋል።

በተለይ ሀገሪቱ ከተጋረጠባት አደጋ ፈጥና እንድትላቀቅ እየተካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ በድል እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በህዝቡ አንድነት ስድስተኛው ጠቅላላ  ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ማድረግ መቻሉን አስታውስዋል።

ሆኖም አዲስ የመንግስት ምስረታ እንዳይካሄድና ሀገር እንዳይረጋጋ ለማድረግ አሸባሪው ህወሐትና ሽኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ግንባር ፍጥረው በንጹሃን ዜጎች ላይ አስከፊና ዘግናኝ ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውን አውስተዋል።

የጋሞ ዞን ህዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም በሞራል፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብ፣ ስንቅ በማዘጋጀትና ደም በመለገስ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪዎቹ ከኢትዮጵያ ምድር ተወግደው ህዝቡ አስተማማኝ ሰላም እስኪያገኝ ድረስ  ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

የምክር ቤቱ ጉባዔ  በ2013 ዕቅድ አፈጻጸም እና በተያዘው የስራ ዘመን ዕቅድ እንዲሁም በጀት ዙሪያ  በመወያየት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም