ሊዲያ ታፈሰ ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ትመራለች - ኢዜአ አማርኛ
ሊዲያ ታፈሰ ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ትመራለች
አዲስ አበባ ነሀሴ 7/2010 ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ፈረንሳይ እየተካሄደ በሚገኘው ዘጠነኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ጨዋታዋን ዛሬ በመሐል ዳኝነት ትመራለች። የዓለም ዋንጫው ከሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል። ዛሬ በስታዴ ዴ ላ ራቢኔ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ በምድብ አራት ጀርመን ከሀይቲ የሚያደርጉትን ጨዋታ ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በመሐል ዳኝነት ትመራዋለች። ሊዲያ ነሐሴ 2 ቀን 2010 ዓ.ም በምድብ አንድ አዘጋጇ ፈረንሳይ ከኒውዚላንድ ያደረገችውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መምራቷ የሚታወስ ሲሆን ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል። በጨዋታው ላይ ሊዲያ ታፈሰ ለኒውዚላንድ ሁለት ተጫዋቾችና ለፈረንሳይ አንድ ተጫዋች የቢጫ ካርድ አሳይታለች። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የማጫወት ልምድ አላት። 16 ብሔራዊ ቡድኖች እየተሳተፉበት የሚገኘው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል።