በግንባር ተገኝተን ድጋፍ ማድረጋችን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች በስጋና በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ለማሳየት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በግንባር ተገኝተን ድጋፍ ማድረጋችን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች በስጋና በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ለማሳየት ነው
ነሀሴ 29/2013 ( ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት በወሎ ግንባር ለተሰለፉ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሌሎች የጸጥታ አካላት 155 ሰንጋ በሬዎችና በጎችን አስረክቧል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪ አቶ አሚን ጁንዲ በወሎ ግንባር ተገኝተን ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሌሎች የጸጥታ አካላት ያደረግነው ድጋፍ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች በስጋና በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ለማሳየት ነው ብለዋል።
በወሎ ግንባር ለሚገኘው ሠራዊትና ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የተበረከቱት 155 ሰንጋ በሬዎችና በጎች ድጋፍ 'አብሮነታችንን ለመግለጽ ነው' ሲሉ ተናግረዋል።
የአማራ ፋኖዎች "የኦሮሞ ደም የኔም ነው" ሲሉ ያሰሙት የአደባባይ ድጋፍ ዛሬም በኦሮሞ ሕዝብ አዕምሮ ውስጥ አለ፤ ይህ ሁለቱ ሕዝቦች አንዱ ለአንዱ ደራሽና የማይነጣጠሉ ወንድማማቾች መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል አቶ አሚን።
በመሆኑም ዛሬ ግንባር ድረስ ተገኝተን ያደረግነው ድጋፍ የሁለቱን ሕዝቦች በስጋና በደም የተሳሰሩና ወንድማማቾች መሆናቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራውን በአማራና በአፋር ክልሎች ያድርግ እንጂ በኦሮሚያም ስውር የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር በአገር ሕልውና ላይ አደጋ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል መንግስት በወሎ ግንባር ያደረገው ድጋፍ የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል።
'አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ ናቸው' እያለ የግጭት ማዕከል እንዲሆኑ ሲያደርግ የነበረው አሸባሪው ህወሓት አሁን ተነቅቶበታል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለዓመታት ሲበዘብዝ የነበረው ህወሓት አሁንም 'አገራችንን እንዳያፈርሳት በተባበረ ክንድ ልንደቁሰው ይገባል' ነው ያሉት።
አቶ በላይነህ አያይዘውም ባለሀብቶች ደሴ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የአንድ ወር ቀለብ፣ ለመከላከያ ሠራዊቱ 5 ሺህ ጥንድ ጫማዎች፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ደረቅ ሬሽን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ደጀን ከሆነው የጸጥታ ኃይል ጎን በመሆን ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ብርጋዴር ጄኔራል ጀማል መሀመድ በበኩላቸው ሕዝቡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ደጀንነቱን አሳይቶናል ብለዋል።
በሕዝቡ ደጀንነት የተነቃቃው የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻም የሽብር ቡድኑን ድባቅ እየመታ መሆኑን ገልጸዋል።
ብርጋዴር ጄኔራሉ "የሽብር ቡድኑን በአጭር ጊዜ በመቅበር የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ሠላሙ እንዲመለስ እናደርጋለን" ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ለሕልውና ዘመቻውና ሕግ ማስከበር ከ263 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።