አምስት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መታወቂያና 25 የተለያዩ የባንክ ደብተሮች ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
አምስት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መታወቂያና 25 የተለያዩ የባንክ ደብተሮች ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ
ነሐሴ 29/2013(ኢዜአ) ፌዴራል ፖሊስ አባላት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ ናሆም አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቀን 25/ 12/ 2013 ዓ/ም በሌሊት ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ አምስት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መታወቂያና ሀያ አምስት የተለያዩ የባንክ ደብተር ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረዉን አቶ ማሃሪ ተከስተ ገ/ኪዳን የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋላቸዉ ተገለፀ፡፡
የግራር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በግለሰቡ ላይ ምርመራ እያካሄደበት እንደሚገኝ የፀጥታና ህግ-ማስከበር የቀጠና 1 ሻለቃ 2 ኃይል 1 አዛዥ ኢ/ር አዲሱ ተሾመ ገልፀዋል፡፡
አሁን ያለውን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር የአሸባሪው ህወሃት ጁንታ ቡድን በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ለመፈፀም የተለያዩ ሰዎችን እየተጠቀሙ ስለሆነና የሽብር ቡድኑን ተግባር ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ስላሉ የፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በመዲናዋ ሌት ተቀን ጠንካራ ፍተሻ እያደረገ እንደሚገኝም አዛዡ ተናግረዋል፡፡
የግራር አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢ/ር ሽፈራው ተሾመ በበኩላቸው የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ በጥምር ባደረጉት ፍተሻ ግለሰቡ በያዛቸው ሀያ አምስት የባንክ አካውንቶች ውስጥ ሁለት ሚሊየን ዘጠኝ መቶ ስልሳ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ብር እና አምስት የአዲስ አበባ መታወቂያ በእጁ ላይ ስለተገኘ ተጨማሪ ምርመራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
ግለሰቡ ምናልባት የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ለማስፈፀም የተንቀሳቀሰ ሊሆን ስለሚችል ምርምራችንን ሰፋ አድርገን እየሰራን እንገኛለን ያሉት ኃላፊዉ ህብረተሰቡም መሰል አጠራጣሪ ጉዳዮችን በሚያይበት ጊዜ በፍጥነት ለፀጥታ አካላት ሪፖርት እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የፌደራል ፖሊስ ማህበራዊ ትስስር ገፅ መረጃ ያመለክታል፡፡