አሸባሪው ህወሃት በአለም አቀፍ ተቋማት ላይ ያደረሰው ዘረፋና ውድመት ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማንቂያ ደወል ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት በአለም አቀፍ ተቋማት ላይ ያደረሰው ዘረፋና ውድመት ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማንቂያ ደወል ነው
ነሃሴ 29፤2013 (ኢዜአ) በመንግስት፣ በግለሰቦችና በአለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ ተቋማት ላይ አሸባሪው ህወሃት ያደረሰው ዘረፋና ውድመት ቡድኑን ለማውገዝ ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማንቂያ ደወል መሆኑን የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት አመለከተ።
የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዮሴፍ ተፈሪ ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪው ህወሃት ወረራ ባደረገባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች በመንግስታዊ፣ መንግስታዊ ባልኑና በአለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት ቡድኑ በመሬት ላይ ምን እያደረገ እንዳለ ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳያ ነው ብለዋል።
ለማሳያነትም አሸባሪው ቡድን በአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት (ዩኒሴፍ) መጋዘኖች ላይ የፈጸመውን ዘረፋ በተመለከተ የዬኒሴፍ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሰጡትን መግለጫ አንስተዋል።
አሸባሪው ቡድን ሰርጎ በገባባቸው የአማራ አካባቢዎች ከፍተኛ ዘረፋና የንብረት ውድመት ማድረሱና ዘረፋውን በአለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ላይም መፈጸሙን ማሳያ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
የደረሰው ውድመትና ዘረፋ ዩኑሴፍ በሁለቱ ክልሎች የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭት በበቂ ሁኔታ እንዳይሰራጭ ማድረጉን ዩኒሴፍ እንደገለጸ አስታውሰው የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያን ህዝብ ለ27 ዓመታት በጭቆና በመብት ጥሰትና በዘረፋ ሲመራ እንደነበር ማስረጃ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ አለም አቀፍ ህግን በመጣስ ህጻናትን ለጦር እያሰለፈ እንደሚገኝና ይህ የሽብር ቡድኑ አካሄድ ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ ለአሜሪካ የማንቂያ ደወል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ የሚያካሂደው ዘረፋ፣ ወድመትና የንጹሃን ጭፍጨፋ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ ስለሚያሳዩ ቀጠናውንም ሆነ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የሚካሄደውን ዘመቻ አሜሪካም መደገፍ እንዳለባት ነው የገለጹት።
አሜሪካ ዴሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በአለም ላይ እንዲሰፍን የምታደርገውን እገዛ በኢትዮጵያም ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲያጎለብት ድጋፏን እንድታደርግ ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።