ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሃት ወንጀለኛ አመራር አባላት ህጻናትን እያስፈጁ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 29/2013(ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ወንጀለኛ አመራር አባላት ህጻናትን እያስፈጁና ትግራይን ትውልድ አልባ እያደረጓት መሆኑን የራእይ ተጋሩ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ሊላይ ሃይለማርያም ተናገሩ።

አሸባሪው ሕወሃት የትግራይ እናቶችን ካለልጅ እያስቀራቸው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አሸባሪው ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የክህደት ጥቃት በመፈጸም መንግስት ተገዶ ወደ ህግ ማስከበር እርምጃ እንዲገባ ማድረጉም ይታወቃል።

የትግራይ ክልል ህዝብ የእርሻ ሥራውን ተረጋግቶ እንዲሰራና የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም በመወሰን ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል አውጥቷል። 

አሸባሪው ሕወሃት ግን የተኩስ አቁም ውሳኔውን ለበጎ ከመጠቀም ይልቅ በማናለብኝነት በአማራና አፋር ክልሎች ውስጥ ግፍ እየፈጸመ ሲሆን፤ በወረራው ህጻናትን በማሰለፍ እያስፈጃቸው ይገኛል።

ለዚህ ደግሞ ውጊያውን ይመራሉ የሚባሉት የአሸባሪው ህወሃት አመራር አባላት እነጄኔራል ጻድቃን ሕጻናቱን በማሰለፍ ለእልቂት መዳረጋቸው በምክንያትነት ይነሳል።

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ጦርነቶች የውግያ ስልትን በማዝረክረክና በማበላሸት፣ የኢትዮጵያ ወጣት ያስፈጁት ጄኔራሎች አሁንም የአሸባሪው ህወሓት ሰራዊት በመምራት ላይ መሆናቸው ይጠቀሳል።

ከእነዚህ መካከል ጄኔራል ወዲ አሸብር እና ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ በጦር ሜዳ ጓዶቻቸው ምስክርነት እና በተግባር እንደተረጋገጠው፣ ጦርነት በማበላሸታቸው ምክንያት የጦር ወንጀለኞች እስከ መባል የደረሱ፤ ከስራቸውም የተሰናበቱ መሆናቸውን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።

አቶ ሊላይ ሃይለማርያም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአሸባሪው የህወሃት ቁንጮ መሪዎች የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በተደረገው የ17 ዓመት የትጥቅ ትግል ወቅት በተደጋጋሚ ወታደራዊ ወንጀል የፈጸሙ ናቸው።

ሕጻናትን በማሰለፍና ለእልቂት በመዳረግ ተጠያቂም ናቸው ይላሉ።

የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ሃይል መሪዎች ከዚህ ቀደም የተሳሳተ አመራር በመስጠት ህዝብ በማስጨረስ የሚታወቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አንዳንዶቹ በዚህ ድርጊታቸው ከዚህ ቀደም ተገምግመው ከስራ መሰናበታቸውን አስታውሰዋል።

 አሁን ላይ በጉና ተራራ ህጻናትን ያስጨረሱበት መንገድ ይህንን እንደሚያሳይ ነው የጠቆሙት።

የሽብር ቡድኑ ወራሪ ሃይል መሪዎች ከቀደመ ስህተታቸው ሳይማሩ "መካናይዝድ ጦር ስለሌለን በህዝብ ማዕበል እናሸንፋለን" በሚል እጅግ በተሳሳተ መንገድ የትግራይ ህጻናትን እያስጨረሱ መሆኑን ነው የገለጹት።

የትግራይ ክልል ህዝብን በጦርነት በማስጨረስ ከግል ጥቅማቸው ውጭ ለህዝቡ ዴንታ እንደሌላቸው በተግባር እያሳዩ መሆኑንም አብራርተዋል።

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ልጆቻቸውን በተደላደለ ሁኔታ እያስተማሩ "በሎም" እያሉ በመቀስቀስ የትግራይ ህጻናትን እያስፈጁ መሆኑንም አቶ ሊላይ ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ በጦርነት ያሰለፋቸው የትግራይ ህጻናት ከሞት ቢያመልጡ እንኳ አደገኛ በሆነ የአደንዛዥ እፅ ሱስ ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የሽብር ቡድኑ "እኔ ከሞትኩ..." በሚል አካሄድ በትግራይ ክልል ብሩህ ተስፋ ያለው ትውልድ እንዳይኖር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብን እንደመያዣ በመጠቀም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ኑሯቸውን እንዲገፉ ማድረጉንም ነው የሚናገሩት።

ይህ አልበቃ ብሎት ለትግራይ እናቶችና ህጻናት የሚሄደውን መድሃኒትና አልሚ ምግብ እየዘረፈ መሆኑንም አንስተው፤ የትግራይ ህዝብ ቆም ብሎ ይህንን የሽብር ቡድን በቃህ ሊለው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የሽብር ቡድኑ በ17 ዓመት የትጥቅ ትግል ሲጠቀምበት የነበረውን ያረጀ ስልት በመከተል የትግራይ ህዝብን እያስጨረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው "ወያኔ እያሸነፈ ነው" በሚል የሃሰት መረጃ ሽብር የሚነዙ ቅጥረኞችም የዚሁ ያረጀ ስልት አካል መሆናቸውን ነው አቶ ሊላይ የሚናገሩት።

ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ዜጋ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ህዝብን የሚያሸብሩ ግለሰቦችን ለጸጥታ አካላት አሳልፎ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም