ቀጥታ፡

አለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በአሸባሪው ህወሃት ለተፈናቀሉ ወገኖች ትኩረት መስጠት አለባቸው...አቶ አገኘሁ ተሻገር

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 28/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማድረግ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘው ተሻገር ጠየቁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ ማምሻውን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት የህወሃት አሸባሪ ቡድን በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር እና ዋግህምኸራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች በፈፀመው ወረራ ምክንያት በርካታ ንጹሃን ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልፀዋል።

በዚህም ለከፋ የምግብ እጥረትና የጤና አገልግሎት አቅርቦት ችግር መጋለጣቸውን አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማትን በማውደምና በመዝረፍ ህዝቡን ለረጅም ጊዜ ችግር ለመዳረግ አቅዶ እየሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።

አሸባሪው ቡድን በከፈተው ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል ከ500 ሺህ በላይ ህዝብ ከመኖሪያ አካባቢው እንደተፈናቀለ ያስረዱት ርዕሰ መስተዳደሩ ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት/ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳደሩ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ክልል እያደረጉ ያሉት የሰብዓዊ ድጋፍ የሚበረታታና የሚደገፍ ነው ብለዋል።

“ነገር ግን በአማራ ክልል በርካታ ህዝብ በአሸባሪው ቡድን ምክንያት ከመኖሪያ ቀየው ተፈናቅሎ ለከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተዳረገ ቢሆንም ሚዛናዊ የሆነ የድጋፍ አሰጣጥ ችግር አለ” ብለዋል።

ስለሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰባአዊ መብት ጉዳዮች በአማራ ክልል አሸባሪው የህወሓት ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ማስረዳትና ረድኤት ድርጅቶች እውነታውን እንዲያውቁት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ የማድረግ ሙከራዎች ቢኖሩም በቂ ያልሆነና መሬት ያልነካ መሆኑን የገለጹት ርእሰ መስተዳደሩ በተለይ ቀጣይ ትምህርት የሚከፈትበት ወቅት በመሆኑ ምግብና ጊዜያዊ መጠለያዎችን በማዘጋጀት በኩል ድጋፍ እንዲደረግ ማስተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለችግር የተዳረገን ህዝብ መርዳት የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን ሰውን የማትረፍ ጉዳይ በመሆኑ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ማርሲ ቪጎዳ በበኩላቸው ከርእሰ መስተዳደሩ ጋር ባደረጉት ውይይት በክልሉ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ በሚገባ እንደተረዱት ገልፀዋል።

በርካታ ህዝብ ምግብ፣ ጊዜያዊ መጠለያ እና አካባቢያዊ ንፅህና እንደሚያስፈልገው ተረድተናል ያሉት ሃላፊዋ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ያስገባ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በዚህ አመት እስከ አሁን ባለው ጊዜ ሰብዓዊ ፈንድ 148 ሚሊዮን ብር በአማራ ክልል ፈሰሰ እንዳደረገ ገልጸው፤ በቀጣይ ሁለት ሳምንታትም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ተጨማሪ ፈንድ ይመደባል ሲሉ አስታውቀዋል።

ማምሻውን በተደረገ የጋራ ውይይት የችግሩን ስፋት በማስገንዘብ ቀጣይ መፍትሄ በሚደረግበት ጉዳይ ዙሪያ መግባባት ተደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም