ዱባይ 2020 ኤክስፖ የኢትዮጵያን እምቅ ሃብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
ዱባይ 2020 ኤክስፖ የኢትዮጵያን እምቅ ሃብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል

ነሀሴ 28/213 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዱባይ 2020 ኤክስፖ የቱሪዝም፣ የባህል፣ የንግድና ኢንቨስትመንት እምቅ ሃብቷን ለዓለም ለማስተዋወቅ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርላት ተገለጸ።
የዱባይ 2020 ኤክስፖ በአውሮፓዊያኑ ጥቅምት 1 ቀን 2021 ይካሄዳል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ "ምድረ ቀደምት የዕድል አገር" በሚል በዱባይ ኤክስፖ ለመሳተፍ ያደረገችውን ዝግጅት አስመልክቶ ለኢዜአ መግለጫ ሰጥቷል።
የሚኒስቴሩ የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኤክስፖው በቱሪዝም፣ በባህል፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ያሏትን እምቅ ሃብቶቿን ለዓለም ለማስተዋወቅ ለኢትዮጵያ ሰፊ ዕድል ይፈጥርላታል ብለዋል።
በኤክስፖው ለእይታ የምትቀርበው "ሉስ" አስቀድማ በቦታው በመገኘት ተመልካቾቿን በመጠባበቅ ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊት አገር መሆኗ፣ የጥቁር ሕዝቦች መለያ የሆነውን የአድዋን ታሪክ፣ የጥምቀት በዓል፣ የአልነጃሺ፣ የቡናና የጤፍ መገኛ መሆኗን ለማስተዋወቅ ዕድል ታገኛለች።
ኤክስፖው በሚካሄድበት ስፍራ የሚገኘው የሉሲ ቅሪተ አካል ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዓለም በስፋት እንዲያውቀው ያደርጋል ብለዋል።
በተለይም የኢንቨስትመንት ዘርፍ እድሎቿን በማስተዋወቅ ባለሃብቶችን ለመሳብ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለኤክስፖው "የእድል መንደር" በሚባለው የማሳያ ቦታ በዱባይ መንግስት የተሸፈነ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ሰፊ ቦታ ማግኘቷን ጠቁመዋል።
በ'ዕድል መንደር' ከ700 ሺህ በላይ የውጭ አገር ጎብኚዎች የኢትዮጵያን ጸጋዎች እንደሚጎበኙ አምባሳደር ምስጋኑ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በኤክስፖው በርካታ የውጭ አገር ዜጎች እንዲጎበኟትና ስኬታማም እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ለኤክስፖው ስኬት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከአንድ ዓመት በላይ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ለስድስት ወራት በሚካሄደው ኤክስፖ ከ191 አገራት በላይ የሚሳተፉ መሆኑ ኢትዮጵያ ጸጋዎቿን ለማስተዋወቅ ያስችላታል ብለዋል።