ለመከላከያ ልጄን መርቄ ልኬያሁ ፤ የወር ደመወዜንና ደም ለግሼያለሁ - ኢዜአ አማርኛ
ለመከላከያ ልጄን መርቄ ልኬያሁ ፤ የወር ደመወዜንና ደም ለግሼያለሁ
ዲላ፤ ነሀሴ 28/2013 (ኢዜአ) ከሀገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለማይኖር ለመከላከያ ልጄን መርቄ ልኬያሁ፤የወር ደመወዜንና ደም ለግሼያለሁ።
ወይዘሮ መሰረት አማረ ይባላሉ፤ እኚህ እናት በዲላ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ ከሚባሉ የአስተዳደር ሠራተኞች መካከል አንዷ ናቸው።
ላለፉት 23 ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ቤተ መጻህፍት ባላቸው የሥራ ድርሻ ለእውቀት የሚተጉ የኢትዮጵያ ልጆችን በታማኝነት አገልግለዋል።
"ሰርተን የኖርንባት፤ ወልደን የከበድንባት ኢትዮጵያ ስትነካና ሰላሟ ሲናጋ ማየት በፍጹም አልፈልገም" ይላሉ።
"ከሀገር ህልውናና ሰላም በላይ የሚበልጥ ነገር ስለሌለ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ልጄ የአብስራ ቴዎድሮስ የመከላከያ ሠራዊት አባል እንዲሆን መርቄ ልኬዋለሁ" ነው ያሉት ወይዘሮ መሰረት አማረ።
ከልጃቸው በተጨማሪ እርሳቸውም ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በግንባር በመሰለፍ ከጠላት ጋር ቢዋደቁ ምርጫቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ወይዘሮ መሰረት በአሁኑ ወቅት በኋላ ደጀንነት ስንቅ በማዘጋጀትና በማቀበል የሀገራቸውን ህልውና ለማረጋገጥ እየተካሄደ በላው እንቅስቃሴ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ወይዘሮ መሰረት ልጃቸው በድል እንዲመለስ መርቀው ከመሸኘት ባለፈ ለመከላከያ ሠራዊቱ ደም በመለገስና የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመስጠትም አጋርነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።
የሀገርን ድንበር የጠበቀውና የትግራይን ህዝብ ለዘመናት ያገለገለውን መከላከያ ሰራዊት ሽብርተኛው ህወሓት ከኋላ ጥቃት መፈጸሙ ሳያንስ የአፋርና አማራ ክልሎችን መውረሩ ይቅር የማይባል አሳፋሪ ጥፋት መሆኑን ነው የገለጹት።
በተለይ አሸባሪ ቡድኑ ለኢትዮጵያ ጠላቶች ተላላኪ ሆኖ የገዛ ሀገሩን መውጋቱ እንዳሳዘናቸው ጠቁመው፣ ቡድኑ እስኪጠፋ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
መላው ኢትዮጵያዊ ከሀገር በላይ ምንም ነገር እንደማይኖር ተገንዝቦ የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ወይዘሮ መሰረት ጥሪ አቅርበዋል።