የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከታክስ በፊት 1 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከታክስ በፊት 1 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኘ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 1ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።
ድርጅቱ የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈጻፃምና የ34ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ እያደረገ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ፣ የሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ከታክሰ በፊት 1 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጸዋል።
በዓመቱ ለማግኘት ከተያዘው እቅድ ጋር ሲነጻጸር በ5 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም ከባለፈው በጀት ዓመት ውጤት ጋር ሲነጻጸር በ13 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ (የመድን ሽፋን ለመስጠት የሚከፈለው የገንዘብ መጠን) የተመዘገበ ሲሆን በዚህም ድርጅቱ ከእቅድ በላይ 17 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
የተመዘገበው የአረቦን መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ23 ነጥብ 5 በመቶ ወይም የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እድገት ያሳየ መሆኑም ተገልጿል።
ከተመዘገበው ጠቅላላ አርቦን 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ወይም 96 ነጥብ 5 በመቶው ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የተመዘገበ ሲሆን ቀሪው 216 ሚሊዮን ብር ከረዥም ጊዜ መድን ዘርፍ የተመዘገበ ነው ብለዋል።
ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለው የአረቦን ገቢ ድርሻም 44 በመቶ እንደሆነ ተገልጿል።
የጉዳት ካሳ ምጣኔን በተመለከተ በዘንድሮው በጀት ዓመት 57 ነጥብ 3 በመቶ አፈጻጸም መመዝገቡን ተገልጿል።
ድርጅቱ በደንበኞች ንብረትና ህይወት ላይ ለደረሰ አደጋ እንዲሁም ህጋዊ ሃላፊነት በአጠቃላይ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈጸሙ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ስራ አመራር የቦርድ አባል ዶክተር ለማ ጉዲሳ፣ እንደ ኢትዮጵያ እያደጉ ባሉ አገራትም ሆኑ በአደጉ አገሮች ውስጥ የመድን ሽፋን አገልግሎት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ያለ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በየአገራቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆነው ያገለግላሉ ከሚባሉት የፋይናንስ ተቋማት አንዱ የመድን ሽፋን የሚሰጡ ተቋማት መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ለማ፤ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም በዚህ ረገድ ሚናውን እየተወጣ እንዳለ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በፍጥነት እየገሰገሰች መሆኑን አመልክተው፤ ድርጅቱ ከእስካሁኑ በተሻለ ብቃትና ሃላፊነት ሚናውን መወጣት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እንዲሳተፍ ጠይቀው በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ በሚጠበቀው የአክሲዮን ገበያ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ከወዲሁ ሊዘጋጅ እንደሚገባ አብራርተዋል።
በበጀት አመቱ ረዥም ወራት ያስቆጠረውና አሁንም ኢኮኖሚውን እየተፈታተነ ያለው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ተጽእኖ ማሳደሩን ድርጅቱ አስታውቋል።
በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች በዚህም ሳቢያ በተለይም በትግራይ ክልል የሚገኙ ቢሮዎች ስራ ለመስራት ያለመቻላቸው ሌላው ችግር መሆኑ ተጠቅሷል።