ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ የኡጋንዳ አቻውን አሸንፏል - ኢዜአ አማርኛ
ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ የኡጋንዳ አቻውን አሸንፏል
አዲስ አበባ ነሃሴ7/2010 በታንዛንያ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የኡጋንዳ አቻውን አንድ ለዜሮ አሸነፈ። በ2011 ዓ.ም በታንዛንያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሴካፋ ዞንን ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ለመለየት ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በታንዛንያ የማጣሪያ ጨዋታ እየተካሄደ ይገኛል። ትናንት በቻማዚ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምንተስኖት እንድርያስ ጎል የኡጋንዳ አቻውን 1ለ0 መርታት ችሏል። በውጤቱ መሰረት ኢትዮጵያ ሶስት ነጥብ አግኝታለች። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 1 በተደረገ ሌላ ጨዋታ ደቡብ ሱዳን የጅቡቲ አቻውን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ምድቡን መምራት ጀምሯል። በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ የምድብ ጨዋታውን ነገ ከቀኑ 11 ሰዓት በቻማዚ ስታዲየም ከጅቡቲ አቻው ጋር ያደርጋል። ከኢትዮጵያና ከጅቡቲ ጨዋታ ቀድሞ ከቀኑ ስምንት ሰዓት የምድቡ መሪ ደቡብ ሱዳን ከኬንያ አቻው ጋር ይጫወታል። የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። በታንዛንያ በመጪው ዓመት በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አገሮችን ለመለየት የማጣሪያ ውድድሩ በሰባት ዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።